ቴሌን ፕራይቬታይዝ የማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው!

በህወሓት የበላይነት ሲዘወር የኖረው ኢህአዴግ አገራችንን ብዙ ነገሮች አሳጥቷታል። ለኔ ግን ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚታየኝ ጉዳት፣ ገና ለገና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚያወራውንና የሚያነበውን ለመቆጣጠር ሲባል፣ መቆጣጠር በሚችሉት ልክ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መገደባቸው ነው። እንደኛ ላለ የመቶ ሚልዮን ህዝብ አገር፣ ሌላውን የልማት እንቅስቃሴ ትኩረት ነፍጎ እነዚህ አገልግሎቶች ላይ ብቻ ሙሉ ትኩረት ቢደረግና ሁሉም ላይ ለማዳረስ ቢሰራ አገራችን የትና የት በደረሰች። ለምሳሌ ጥቂቶችን እንመልከት፥

  1. ዜጎች ህይወታቸውን ለመቀየር የግድ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ለመዝለቅ ዓመታትን መፍጀት የለባቸውም። በኢንተርኔት የሚሰጡ አጫጭር ኮርሶችን በራሳቸው ጊዜ ተምረው፣ ስራ መፍጠር ይችላሉ። ስንት ዓመት አባክኖ ያውም ያለፍላጎት በተመደበበት የትምህርት ዘርፍ ተመርቆ ወረቀት እየያዘ በየቢሮ ደጅ ከመጥናት፣ ሆቢንና አቅምን ያገናዘበ አጫጭር ኮርስ በራስ ተነሳሽነት ወስዶ ስራ መፈለግ ወይም መፍጠር የተሻለ ውጤታማ ነው። (ይህ በተለይ በትምህርት መግፋት ለማይፈልግ ሰው አዋጭ አማራጭ ይመስለኛል።)
  2. በአገራችን የሰው ጉልበት ርካሽ እንደመሆኑ መጠን የውጪ ኩባንያዎች ሳይቀሩ በስልክና በኢንተርኔት የሚሰጡ አገልግሎቶቻቸውን በአገራችን ለተቋቋሙና ለሚቋቋሙ ኩባንያዎች አውት ሶርስ ባደረጉ ነበር። ይህ በሌላ አገር (በነ ህንድ) መልቲ ቢልዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ነው።
  3. ፈጣን የመረጃ አገልግሎት በገበያ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ምርምር፣ በባንክና ፋይናንስ አገልግሎት፣ ህዝብ በሚያዘውትርባቸው የአገልግሎት መስጫ ተቋማት (ህክምና፣ መዝናኛ፣ ጸጥታ፣ ወዘተ) ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ በመርዳት፣ በአገሪቱ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አወንታዊ ሚና መጫወት በቻለ ነበር።
  4. በዛሬ የቴክኖሎጂ እምርታ፣ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ሳያስፈልጋቸው ብዙ ነገር ከአንድ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚችሉበት ጊዜ ላይ ነን። ዳያስፖራ ተቀምጠው በአገራችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ሚድያዎችን ማየት በቂ ምሳሌ ነው። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከትራንስፖርት ወጪ፣ ከጊዜ ውስንነት፣ ከቢሮክራሲ፣ ከኢሚግሬሽን ፖሊሲዎች፣ እና ሌሎች መሰል እንቅፋቶች ታደገውን የግብይት ወጪያችንን (transaction costs) ወደ ኢምንት ያወረዱ ናቸው። ይህ ከመጠን በላይ የልማት እንቅስቃሴን ያፋጥናል። የአንድ አገርን ህዝብ ያስተሳስራል። ሪስክ የመውሰድ ድፍረትን ያላብሳል። ለአዳዲስ ግኝቶች በር ይከፍታል።
  5. እጅግ በጣም በጣም ብዙ፣ ተዘርዝረው የማያልቁ ቁልፍ ጥቅሞችና ፋይዳዎች አሉት። ይህን የተረዱ መንግስታት ልጆቻቸውን ገና ከጅምሩ ከኮምፕዩተር፣ ከታብሌትና ከስማርት ፎን ጋር ያስተዋውቋቸዋል። የኔ ልጅ በሚቀጠለው ዓመት ሁለተኛ ክፍል ትጀምራለች። እያንዳንዱ ተማሪ የግሉ አይፓድ ይሰጠዋል። አይፓዱ ማስታወሻ ደብተራቸው ነው፣ መጽሃፋቸው ነው፣ ላይብሬሪያቸው ነው፣ ጌም እየተጫወቱ የሚማሩበት ነው፣ ፕሮግራሚንግ የሚጀምሩበት ፕላትፎርም ነው፣ ወዘተ ምክንያትም ፊቸሩ የተቆራኘው ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንደሆነ ስለሚታወቅ። ለእያንዳንዱ ተማሪ አይፓድ መስጠት አገራችን አትችል ይሆናል፣ ነገር ግን ራሱን ችሎ ለመማር የተዘጋጀውን ሜዳውን ብናመቻችለትስ?

ዛሬ በክፍለሀገራት የሞባይል ዳታ መልቀቁን ሰማሁ። ይህ ጥሩ ጅምር ነው። ነገር ግን መንግስት ሊገፉበትና አገልግሎቱን ሊያሰፋው ይገባል። መንግስት ብቻውን ስለማይችለው ቴሌን ፕራይቬታይዝ የማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው። አገራችንን እስከወዲያኛው እንዳንቀየር ኢህአዴግ የቆለፈብንን በር አሁን ክፈቱልን።

[fbcomments]

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *