ራዕይ

ያለፈውን ታሪካችንን ዛሬ ያለቅጥ በመመልከት መከራከር የሚቀናን ያክል፣ ወደፊት መመልከት የሚቀናው ትውልድ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምህዳር ተቆጣጥሮት ማየት ነው። በጎም ይሁን መጥፎ የመጣንበት መንገድ ያስተሳሰረን መሆኑ ባይካድም፣ በይበልጥ የሚያስተሳስረን ደግሞ በጋራ የምንፈጥረው ነገአችን (our future) ነው። ይህን ራዕይ የሚያንጸባርቁ ሃሳቦች በዚህ ድረገጽ ላይ ይነሳሉ። ድረገጹ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃዎችንና የጦማሪውን የግል እይታዎችን ለማካፈል ይሞክራል።

ዓላማዎች፦

• ቀዳሚው ዓላማ በመረጃና ማስረጃ የተደገፉ ወቅታዊ ጎዳዮችን በማንሳት ለውይይትና ለክርክር በር መክፈት ነው።
• ሁለተኛው ዓላማ ከተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችና የመረጃ ድረገጾች የተገኙ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መረጃዎች በተለየ መልኩ ለአንባቢዎች ማቅረብ ነው።
• ሶስተኛው ዓላማ የአንባቢው ተሳትፎ በፈቀደ መጠን አዳዲስ መረጃዎችን (polls) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በማሰባሰብና ውጤቱን በማጋራት ለዳበረ ውይይት በር መክፈት ነው።

ጥቂት ስለ ጦማሪው

በትውልድ፣ በዜግነትና በብሔር – ኢትዮጵያዊ፤ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት።

ትምህርት –

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባና በአስመራ እንዲህውም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአክሱም የተከታተለ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርቱን በአምቦ እርሻ ኮሌጅ፡ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፡ በኖርወይ የተፈጥሮ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ (Norwegian University of Life Science (NMBU)) እና በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ (University of Oslo (UIO)) ተከታትሏል። የከፍተኛ ትምህርቱን በጠቅላላ እርሻ (ዲፕሎማ)፣ በአካባቢና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንዲህውም በኢኮኖሚክስ (የመጀመሪያ ዲግሪዎቹን)፣ በአካባቢ ጥበቃና አስተዳደር (Environmental Governance) እና በኢኮኖሚክስ (Development Economics) (ሁለተኛ ዲግሪዎቹንን) የተከታተለ ሲሆን “በጂኦማቲክስ” (Geomatics (GIS & Remotes Sensing)) የትምህርት ዘርፍ ደግሞ የአንድ ዓመት የድህረ ምረቃ ፕሮግራም በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ተከታትሏል። የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን ከተለያዩ ተቋማትም ወስዷል ።

ስራ –

ቀደም ሲል ጎልጎል ራያ ተብሎ ይጠራ በነበረ ፕሮጀክት ስር እና በግብርና ጽህፈት ቤት ስር በተለያዩ የስራ ሃላፍነቶች (ከልማት ሰራተኛ ጀምሮ እስከ ዲፓርትመንት ኃላፊ ድረስ) በማይጨው አካባቢ ሰርቷል። በተጨማሪም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ አመት በአስተማሪነት ሰርቷል። ባሁኑ ሰዓት በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ውስጥ Research Assistant ሲሆን ይህ የስራ ዕድል ከበርካታ ዓለም ዓቀፍ ባለሞያዎች ጋር ከማገናኘት ባሻገር በፖለቲካል ሳይንስ በተለይም በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካል ሂስትሪ (poltical history) ግንዛቤውን ለማስፋት እድል እንደፈጠረለት ይናገራል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በዚህ ስራ ከተሰጡት የስራ ሃላፊነቶች መካከል ዋንኞቹ፡ ከ1789 እስከ 1920 እኤአ ድረስ የነበሩ የ70+ አገራት ስርዓተ-መንግስት፣ የምርጫ ሂደት፣ የፓርላማ መዋቅር እና የክልል መንግስታት ዴሞክራሲያዊነት እና ሌሎች ተዛማጅ ፖለቲካዊ ተቋማትን በተመለከተ ከታሪክ መዛግብትና ቀድሞ ከተሰሩ ጥናቶች አዲስ መረጃ ማሰባሰብ እንደሚገኝበት ይገልጻል። ከዚህ በመነሳት ከሌሎች አገራት የፖለቲካ ታሪክ መማር ወይም መዳሰስ የሚገባን ነገር ይኖራል ብሎ ሲያስብ በጽሁፎቹ ሊዳስሳቸው ይሞክራል።