ከጥንት ሮማውያን እስከ ትዊተር የደረሰው የ# ምልክት

ቢቢሲ አማርኛ

 

በዘመነኛው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ”ሃሽታግ” (#) የምንለው ምልክት በስፓኒሽ ቋንቋ ብዙ ስሞች አሉት። ፓድ፣ ኑሜራል፣ ኩዋድሪሎ፣ ግሪላ እና ጋቶ ደግሞ ጥቂቶች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውም ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር በተገናኘ ሲሆን፤ በተለይ ”ትዊተር” የተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ የተለያዩ ሃሳቦችና እንቅስቃሴዎች የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማድረግ ይጠቀምበታል።

ምንም እንኳን የ# ምልክትን እ.አ.አ በ2007 ላይ ትዊተር መጠቀም ቢጀምርም፤ የምልክቱ አመጣጥ ግን ወደ ጥንታዊ ሮማ ይጓዛል።

በጊዜውም ጥንታዊ ሮማውያን የአንድን ነገር ክብደት ለመግለጽ ይህንን ምልክት ይጠቀሙ ነበር።

እ.አ.አ በ1950ዎቹ በአሜሪካ የሚገኘው ”ቤል ላብስ” የተሰኘው የሳይንሳዊ ምርምር ተቋም የሚሽከረከሩ የስልክ መደወያዎችን በማስቀረት የምንደውልበትን ቁጥር በስልኩ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ አለ።

በ1968 ደግሞ ከመደወያ ቁጥሮቹ ጎን ለጎንም የተለያዩ ጥቅሞች ያሏቸው ምልክቶችን አብሮ አስተዋወቀ። ይህ # ምልክትም ከእነዚህ መካከል ነበር።

ምልክቱ ምን ያህል ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ለማጣራት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት አብዛኛዎቹ የስልክ ተጠቃሚዎች ይህን # ምልክት መጠቀም እንደሚያስደስታቸውና ለመጠቀም ቀላል እንደሆነም ገልጸዋል።

በወቅቱም ”ኦክቶትሮፕ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።

በዚህ መልኩ የተጀመረው የምልክቱ አጠቃቀም ወደ ዘመናዊው አለም ሲመጣ ቀስ በቀስ ብዙ ትርጉሞችን መያዝ የጀመረ ሲሆን፤ እንዲያውም የኮምፒውተር መተግበሪያዎች ላይ ሚስጥራዊ መልክቶችን እስከመወከል ደረሰ።

በአሜሪካና በእንግሊዝ በብዛት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ይህ ምልክት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በመላው ዓለም ታዋቂነትን ማትረፍ ከጀመረ አስራ አንድ ዓመታትን አስቆጥሯል።

እ.አ.አ በወርሃ ነሃሴ 2007 ነበር የቀድሞው የጉግል እና የኡበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሪስ ሜሲና ምልክቱን በመጠቀም በተለይ ደግሞ ትዊተር ላይ የተለያዩ የመወያያ ሃሳቦችን ወደፊት ለማምጣት ጥቅም ላይ እንዲውል ሃሳቡን ያቀረበው።

ትዊተር 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ሜሲና ለቢቢሲ እንደተናገረው ምልክቱ ወደ ጥቅም ከመምጣቱ በፊት ሰዎች ሃሳቦቻቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተበታተነና ለተጠቃሚዎች አስቸጋሪ ነበር።

ይህ # ምልክት ወደ ጥቅም ከመጣ ወዲህ ግን ተጠቃሚዎች ምልክቱን ካስቀመጡ በኋላ የሚፈልጉትን ርዕስ በመጻፍ ሌሎች ሰዎች ስለጉዳዩ ያጋሩትን ሃሳብ ማግኘት ይችላሉ። ይህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ የራሳቸውንም ሃሳብ ለሌሎች እንዲያጋሩ ይረዳቸዋል።

ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም የሌለብዎት ሰአት መቼ ነው?

ማህበራዊ ሚዲያዎች በአብዛኛዎቻችን እንቅልፍ ስርአት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው። ታዲያ እነዚህን ማህበራዊ ሚዲያዎች ገሸሽ ማደረግ ያለብን ሰአት የትኛው ነው?

የዘመኑ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ ለተመለከተ ወዴት እየሄድን ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል?

ባደጉት ሃገራት የሚገኙ ከ11 እስከ 15 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በአማካይ ከ6 እስከ 8 ሰአታትን ማህበራሚዊ ሚዲያዎች ላይ ወሬዎችን ሲቃርሙ ያሳልፋሉ።

አንድ የተሰራ ሌላ ጥናት ደግሞ በእንግሊዝ የሚገኙ እድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች በእንቅልፍ ከሚያሳልፉት ጊዜ በበለጠ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ያሳልፋሉ ይላል።

አሜሪካ ውስጥ ደግሞ ከ13 እስከ 18 እድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ታዳጊዎች 70 በመቶ የሚሆኑት ‘ስናፕቻት’ የተባለውን የማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሲሆን ‘ኢንስታግራም’ የተባለውም ማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ተከታዮች አሉት ተብሏል።

በዓለማችን የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ቁጥር ከሶስት ቢሊየን በላይ እንደሚሆን ይገመታል። አብዛኛዎቻችን ደግሞ ከአንድ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን እንጠቀማለን።

በአማካይም ከ2 እስከ 3 ሰአት በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እናጠፋለን።

በማህበራዊ ሚዲያዎችና በድብርት መካከል ያለውን ግንኙነት ስናስብ ሁለት አይነት ተጽእኖ አንዳለው ማስተዋል ይቻላል። የመጀመሪያው ድብርትን ለማራገፍ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚጫወቱት ሚና ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎችን አብዝተን ስንጠቀም የሚፈጠርብን ድብርት ነው።

ነገር ግን በቅርቡ 2000 ሰዎችን አሳትፎ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት ማህበራዊ ሚዲያዎች አሉታዊ ተጽእኗቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ያሳያል።

በጥናቱ መሰረት ማህበራዊ ሚዲዎችን አብዝተው እንዲጠቀሙ የተደረጉት ተሳታፊዎች ድብርት፣ ጭንቀትና በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አለመፈለግን የመሳሰሉ ምልክቶች ታይተውባቸዋል።

”ምናልባትም ማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ከጓደኞቻቸው ጋር እየተገናኙ ወይም መልእክት እየተለዋወጡ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከየትኛውም ጓደኛቸው ጋር ፊት ለፊት ተያይተው አያወሩም” ይላሉ በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የመገናኛ ብዙሃን ጥናት፣ ቴክኖሎጂና ጤና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ብራያን ፕሪማክ።

ፕሪማክና የጥናት ቡድናቸው 1700 ወጣቶች ላይ በሰሩት ጥናት መሰረት ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀምት ሰአት የሚያሳድርብንን የጫና አይነት ይለያየዋል።

እንቅልፍ ከመተኛታችን ከ30 ደቂቃ በፊት ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ከሆነ ጥሩ ያልሆነና በጣም አጭር እንቅልፍ እንድንተኛ ሊያደርገን ይችላል ይላሉ ፕሪማክ።

ይህ የሚሆነው ደግሞ ከስልካችን የሚወጣው ሰማያዊ ጨረር ‘ሜላቶኒን’ የተባለውን በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን ንጥረ ነገር ስለሚጎዳው ነው። ይህ ንጥረ ነገር ደግሞ ዋነኛ ስራው የእንቅልፍ ሰአት ሲደርስ እንድንተኛ ማድረግ ነው።

”ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከመተኛታችን በፊት በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንመለከታቸው ዜናዎችና ሌሎች መረጃዎች ብዙ ሃሳብ ያመጡብናል። በመተኛችን ሰአት ስለመረጃዎቹ ማሰላሰል እንጀምርና እንቅልፋችን እያየነው ያመልጠናል” ሲሉ ያብራራሉ ፕሪማክ።

ከዚህ በተጨማሪ ከእንቅልፍ በፊት የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ አንቅልፍ እንድንተኛ ማድረጉ እሙን ነው። ብዙ ጊዜያችንን በማህበራዊ ሚዲያ ባሳለፍን ቁጥር ደግሞ የእንቅስቃሴ ሰአታችን ይቀንሳል ማለት ነው። ይህም ሌላ ችግር ነው።

ብዙ ተጠቃሚዎች ባሏቸው እንደ ‘ፌስቡክና’ ‘ኢንስታግራም’ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች ጥሩ ህይወት እየመሩ እንደሆነ የሚያሳዩ ምስሎችን በለጠፉ ቁጥርና ስለጎበኟቸው ቦታዎች ባወሩ ቁጥር፤ የእኛን ህይወት ከእነሱ ጋር እያወዳደርን የምንጨነቅ ከሆነ ወደ ድብርትና እነቅልፍ ማጣት መውሰዳቸው ደግሞ ሌላኛው የማህበራዊ ሚዲያ ጉዳት ናቸው።

የእንቅልፍ ሰአታችን በቀነሰ ቁጥር ደግሞ ለልብ በሽታዎች ያለን ተጋላጭነት ይጨምራል፤ የስኳር በሽታና አላስፈላጊ ውፍረትን የመሳሰሉ ችግሮችንም አብሮ ይዞ ይዞ ይመጣል።

በዚህ በጣም ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ ታዳጊዎቹ ናቸው። ምክንያቱም ሰውነታቸው ገና እድገቱን ያልጨረሰ እንደመሆኑ እንቅልፍ ማጣት ብዙ የሰውነት ስርአቶችን የማዳከምና የማጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነው።

ስለዚህ ይላሉ ባለሙያው፤ ቤተሰቦችና መምህራን ታዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለሚያጠፉት ጊዜ ሊጠይቁና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል።