መለስ ዜናዊን በብዙ ምክንያት እጠላው ነበር። ይህን ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ ማምጣቱ፣ ከኔ በላይ አዋቂና ብቁ የለም ብሎ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለቱ፣ ይህን ለማድረግ የተጓዘበት ርቀት (የሚመራው ድርጅት በሀሳብ ድርቅ እስኪጠቃ ድረስ የተማረ ሰው የማያስጠጋ መሆኑ)፣ ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ማንም የማይክደውና የሚደነቅበት ብቃት ደግሞ ነበር። የኢኮኖሚክስ እውቀቱ ከባድ ሚዛን (ወርልድ ክላስ) ነበር።

መለስእነ ጆሴፍ ስቲግልዝ (በኢኮኖሚክስ ኖቤል ተሸላሚዎች)፣ እነ ፒተር ጊልስ (አዋርድ ዊኒንግ ጋዜጠኞች)እና ሌሎችም ብዙ ግዜ መስክረውለታል። መጽሀፋቸው ላይ አንድ ምእራፍ ሙሉ ሰጥተው ትንታኔውን ከትበውታል፣ አድናቆታቸውን ችረውታል። መለስ የተደነቀበት የኢኮኖሚክስ እይታ “በድሀ አገር ሙሉ በሙሉ ነጻ ገበያ መፍቀድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል”፣ “ሉአላዊነታቸውን ያሳጣቸዋል”፣ “በውጭ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ቁጥጥር ስር ይወድቃሉ” በሚለው አቋሙ ነው። በኢትዮጵያ ይህን ከምፈቅድ እንደኤሊ ቀስ እያልን ብናዘግም እመርጣለሁ። የሚል ጽኑ አቋሙ ነበረው። በተለይ ጆሴፍ ስትግልዝ ከባንክና ከመሬት ሊበራላይዜሽን ጋር በተያያዘ በአንዲት ሌሊት ብዙና ጠንካራ የመከራከሪያ ጭብጦችን ማንሳቱ በአግራሞት ያነሳል። በተለይ ከኢስት ኤሽያ ክራይስስ ብዙ ምሳሌዎችን በመጥቀስ፣ ካገሩ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስደማሚ ክርክሮችን ማንሳቱ ያወሳል።

ዛሬ ሴንሲብል የሆኑ የአሜሪካ ምሁራን ጆሴፍ ስቲግልዝን ጨምሮ የነጭ ካፒታሊዝም ተቃዋሚዎች ናቸው። ዘ ኢኮኖሚስት በተደጋጋሚ የሚጽፋቸውን አርቲክሎች ላነበበ፣ የስካንዲኔቭያን ዓይነት ኢኮኖሚክ ሞዴል ተግባራዊ ለማድረግ የከጀሉ ይመስላል። በተደጋጋሚ በሚያስተዋውቁት አንድ የሽፋን ገጻቸው “ሶሻሊዝም የነገ ርእዮተ ዓለም” የሚል ምጸት ይዘው ቀርበዋል። የአየር ለውጥ የሚያሳስባቸው ኢኮኖሚስቶችና ፖለቲካል ሳይንቲስቶች እንዲህውም የአካባቢ ጥበቃ አድቮኬሲ ቡድኖችና ፈላስፋዎች እንደነ Naomi Klein ፣ Noam Chomsky፣ Slavoj Žižek አለምን ለማዳን ከካፒታሊስት (ነጻ ገበያ) ስርዓት መውጣት አለብን፣ ሲሉ ላንቃቸው እስኪነቃ ድረስ ያቀነቅናሉ።

በአንጻሩ አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ማንም ሳይመርጠውና ይሁንታውን ሳይሰጠው፣ የኢትዮጵያን ህዝብና አገር ወክሎ የሚወስናቸው ውሳኔዎችና የሚፈጽማቸው ውሎች፣ እስከዛሬ ድረስ መለስና ኢህአዴግ አስከብረዉት የነበረ የኢኮኖሚ ድንበር የሚያስደፍር ነው። ይህ ድርጊቱ የአገሪቱን ሉአላዊነት በረጋግዶ አሳልፎ ከመስጠት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የአለም ካፒታሊስት ስርዓት አራማጅ ወደ መሀል እየመጣ ባለበት፣ በቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዓት(ቅድሚያ ላገር ውስጥ ባለሀብት ቦታና ትኩረት በመስጠት) ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ያሉ አገራት በተበራከቱበት፣ አብይ ብቻውን ወደዚህ መንደር የሚያደርገው ግስጋሴ ከእንጭጭ ጭንቅላት የመነጨ ከሰራቸውና እየሰራቸው ካሉ ክፋቶች ሁሉ የከፋ ተግባር ነው።

አዎ ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያስመዘገበው እድገት አለ። ከሚያገኘው ድጋፍና ብድር ጋር የማይመጣጠን ዝቅተኛ እድገት ቢሆንም ለውጥ ነበረ። ኢህአዴግ የሚወገዘው እድገት ባለማስመዝገቡ ሳይሆን፣ ህዝብን የዛ እድገት ተጠቃሚ አለማድረጉና የተመዘገበው እድገት ለጥቂቶች ብቻ የተደፋ ዳቦ በመሆኑ ነበረ። በሌላ አነጋገር በግልጽም ይሁን በድብቅ እየዘረፉ ራሳቸውንና በዙሪያቸው ያሉትን ብቻ እየጠቀሙ ሌላውን አድኽይተው ለመግዛት መሞከራቸው ነበር ትልቁና ዋነኛ ስህተታቸው። ይህን ስህተት አብይ በቀላሉ ማረም ይችል ነበር። ገበያውን በረጋግዶ ለውጭ ኮርፖሬሽኖች መስጠት አያስፈልገውም ነበር።

ህዝብን የእድገቱ ተጠቃሚ ለማድረግና የተሻለ እድገት እንዲኖር ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር መዘርጋት ብቻ ነበር የሚያስፈልገው። በሌላ አነጋገር በነጻ ገበያ ስም ያገር ሀብት ከመቸብቸብ በፊት የህግ የበላይነት ማስከበር መቅደም ነበረበት። ሙስኞችን ለህግ ማቅረብ፣ የህዝብ ንብረት ማስመለስ፣ ነጻ ሚድያ፣ ነጻ የፍትህና የኦዲት ስርዓት መዘርጋት ወዘተ በማስቀደም ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቅደም ነበረበት። በሒደት የአገር ውስጥ ባለሀብት አቅም ካካበተ ብኋላ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ነው ዛሬ እየተወሰደ ያለው።

ከፈረሱ በፊት ጋሪው ቀድሟልና ወደ ተግባራዊነቱ ከመሸጋገሩ በፊት የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ሰውዬ አካሔድ ላይ ልጓም ቢጤ ቢያኖሩለት ይመከራል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *