ታላቁ ንቅናቄና የህውሓት ግብረመልስ

በኔ እምነት የኢትዮጵያውያን የነጻነት ንቅናቄ እማይቀለበስ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከዚህ ብኋላ መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ ሳይመጣ ህዝቡ ከንቅናቄው ያፈገፍጋል የሚል እምነት የለኝም። ለዚህም ነው ታላቁ ንቅናቄ ለማለት የደፈርኩት። በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት 25 ዓመታት ካየነውና ከራሳቸው አንደበት ከሰማነው፡ ህውሓት ስልጣኑን በዚህ መንገድ በቀላሉ ይለቃል ብዬ አላምንም። ዛሬም ድረስ በነ ዓይጋ ፎረምና ትግራይ ኦን ላይን ላይ የምናነባቸው ነገሮች “እኛ ካልመራን አገሪቱ ትበታተን” የሚል እንድምታ ያላቸው ጽሁፎችን ነው። ይህም የሚያሳየው የፖለቲካ የበላይነቱን እንደተቆናጠጡ በስልጣን ላይ ለመቆየት አሉ የተባሉትን አማራጮች በሙሉ አሟጠው እስከመጠቀም ድረስ ሊዘልቁ እንደሚችሉ እንጂ ለህዝብ ጥያቄ ጆሮ አይሰጡም።

የመጨረሻ የሚባለው ስልጣንን የማስጠበቂያ መንገድ ደግሞ ሲቪል ዋር በመቀስቀስ – የነ ሲርያን መንገድ መከተል ነው። ባለፈው አንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር አልጄዚራ ቀርቦ እንዳለው “There are some parallels with Syria.” ለዚህ ማረጋገጫ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ባደባባይ ወጥቶ የሚናገራቸውን ማዳመጥ በቂ ነው። “ምንም ተጨማሪ ቤንዚን ሳያስፈልጋቸው እሳትና ጭድ የሆኑ ሃይሎች (አማራና ኦሮሞ) ተቀራርበው መስራታቸው የሚጠበቅብንን ስራ እንዳልተወጣን ያሳያል” ብሏል። ኢትዮጵያ የተደገሰላት ነገር በአግአዚ ጥይት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን መገበር ብቻ ሳይሆን በሺዎች ምናልባትም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ንጹሃን እርስ በእርስ የሚተላለቁበት ሲቪል ዋር ይመስላል።

ታድያ ምን በጀን?

እንግዲህ ህዝብ መሰረታዊ ለውጥ ሳይመጣ ከትግሉ ወደ ኋላ የማይል ከሆነና ህውሓት ስልጣኑን ለማስጠበቅ ማንኛውም እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ለቀጣዩ ጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት በርካታ የሰው ህይወት ሊጠፋ ይችላል ማለት ነው። ከሚሞተው በተጨማሪ ብዙ የመቁሰል አደጋዎች ይኖራሉ። ይህም መሰረታዊ የፖለቲካ ክፍፍሎችን በሁለቱ ወገን ይፈጥራል።

አንደኛው የኢህአዴግ ፓርቲን የበለጠ ይሰነጥቀውና ክፍፍሉ ጎልቶ እንዲወጣ ያደርጋል። ባንድ በኩል በህውሓት የፖለቲካ የበላይነትና ትዕዛዝ ሰጪነት ህዝብ እየተወሰደበት ያለውን እርምጃ የሚቃወሙና በቃ! የሚል አንጃ ሲፈጠር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ዓይነት እርምጃ ካልወሰድን ህልውናችን አደጋ ላይ ነው የሚል የልሂቃኑ አንጃ ይፈጠራል። ጥልቅ ክፍፍሉም ጎልቶ ይወጣል። ከድርጅቱ ነባራዊ እውነታ አንጻር ስንመለከተው የጦር አዛዥነቱን በበላይነት የተቆጣጠሩት የአንድ ቡድን አባላት በመሆናቸው የያዙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ጉልበት እንደተሻለ አማራጭ የሚመለከቱ ሲሆኑ ከህዝብ ወገን የሚሆኑት ደግሞ ባብዛኛው ትዕዛዝ የማስፈጸም (ተላላኪነት) ሚና የነበራቸው የመከላከያም ሆነ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ሃይል በትዕዛዛቸው ስር የሌላቸው ይሆናሉ።

ታድያ እዚህ ላይ ማጤን ያለብን ነገር አለ፤ ይኸውም ጦሩን በመምራት ረገድ የበላይነቱን የተቆናጠጡት ያንድ ቡድን አባላት ናቸው ማለት ጦሩን እንዳሻቸው መዘወር ይቻላሉ ማለት አይደለም። የድርጅቱ ክፍፍል ሰራዊቱ ድረስ ዘልቆ የመግባት እድል አለው። ሰራዊቱ የህዝብን ጥያቄ ማንሳት መጀመሩ በተለያዩ ቦታዎች ታይቷል። ስለሆነም የጦር አዛዦቹ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበትና በህዝብ ላይ እርምጃ ከመውሰድወደ ኋላ የማይል ክፈለ ጦር ባስቸኳይ ሊመሰርቱ (ወይም ካሉት መካከል የተወሰኑትን ሊያጠሩ) ይችላሉ። ይህ የራሱ የሆነ ግብዓት ይፈልጋል። ግብዓቱን የሚያቀርብለት ምክንያትም መፈጠር ይኖርበታል።

ሁለተኛው ተቃውሞውን ከሚያሰማ ከህዝቡ መካከል ወይም ተቃዋሚ ነኝ በሚለው መካከል ልዩነት ይፈጠራል። የመጀመሪያው ወገን የጀመረውን ትግል ማንኛውንም ዓይነት መስዋእትነት ከፍሎ ዳር ለማድረስ ወደ ኋላ ሳይል በጽናት መግፋት እንደ ቁልፍ የትግል ስልት የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ወገን ደግሞ ‘በባዶ ሜዳ መሞት ይብቃና እየገደልን እንሙት’ የሚልና ምናልባትም ወደ ሲቪል ዋር ሊያመራ የሚችል እርምጃ ሊወስድ የሚችል ሃይል ይሆናል። የመጀመሪያ ወገን ሁሉንም አቅፎና ደግፎ ንቅናቄውን በጽናት የሚገፋ ሲሆን ሁለተኛው ወገን ስርዓቱን የተበቀለ መስሎት ሲቪሊያን ላይ (በብሄራቸው ምክንያት) እርምጃ መውሰድ እንደ ቀዳሚ የትግል ስልት ሊያይ የሚችል ይሆናል። ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ አይወጣም በሚል ስልት የሚመራው የመጀመሪያ ወገን የትግል መሪነቱን ከልተቆናጠጠ በቀል እንደ ቁልፍ ትግልና ለነጻነት ጥያቄ እንደ ብቁ ምላሽ በሚመለከት ሁለተኛው ወገን ትግሉ ይቀለበሳል።
ምን በጀን

የክፍፍሎቹ እንድምታ

በጉልበቱ የሚተማመነው የኢህአዴግ አንጃና በበቀል የሚያምነው የህዝብ አንጃ ትግሉን በበላይነት ከመሩት አገሪቱ ወደ መፍረስ አደጋ አቀናች ማለት ነው። ሌላ ሩዋንዳ ሌላ ቦሲንያ ሌላ ሲርያ የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ ይሆናል። በበቀል የሚያምነው የህዝብ አንጃ ዘር አነጣጥሮ ለመበቀል ሲሞክር በጉልበት ለሚተማመነው የኢህአዴግ አንጃ የሚፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ይተባበረዋል ማለት ነው። የኢህአዴጉ አንጃ በዘሩ ምክንያት የሚጋልበውና የሚያዘው ሰራዊት መፍጠር ይችላል ማለት ነው። ሌላ ሲርያ የመሆን ዕድላችን ሰፊ የሚያደርገው ይህ ነው።

ከዚህ ይልቅ ሁለተኛው የኢህአዴግ አንጃና የመጀመሪያው የህዝብ አንጃ ከተደማመጡና ከተደጋገፉ አገሪቱ ተስፋ ወዳለው የለውጥ ጎዳና ልታመራ ትችላለች። እነዚህ ሁለቱ ሃይሎች በመደማመጥ ትግሉን በበላይነት መምራት የግድ ይኖርባቸዋል።

መደማመጥና መደጋገፍ የሚችሉት እንዴት ነው?

 1. በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ከህዝብ ወገን የሆኑና የወያኔ ስርዓት እየወሰደ ያለውን ጸረ ህዝብ እርምጃ የሚያወግዙ አመራሮች/ካድሬዎች ባደባባይ ወጥተው በግልጽ መናገር ሲጀምሩ;
 2. ድርጅቱ ውስጥ ሆነው ተቋውሟቸውን ለሚያሰሙና ከህዝብ ወገን ለቆሙ የኢህአዴግ አባላት ህዝብ ከጎናቸው ቆሞ አለሁ ሲልና መከታ ሲሆናቸው;
  • ለምሳሌ እንደ አቶ ገዱ ዓይነት የህዝብ ወገን መሆናቸውን ያሳዩ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባሎች፤ ህዝብ ለነኮለኔል ደመቀ ያሳየውን ያህል መከታነት ካሳየ ሌሎች ገዱዎች ከፓርቲው አፈንግጠው የህዝብን ትግል በግልጽ እንዲቀላቀሉ ይረዳል።
 3. ተስፋ የቆረጡ ሰዎች (ከውጭም ሊሆን ይችላል ካገር ውስጥ) ህዝብ ለሚወሰድበት እርምጃ አጸፋዊ ምላሽ በሲቪልያን ንብረትና ህይወት ላይ እንዲወስድ ጥሪ ሲያቀርቡ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ሲቻል;
  • ከፓርቲው ያፈነገጡ ሰዎችን ተቀብለን ስናስተናግድ ፓርቲውን የምናዳክመውን ያህል በሲቪልያን ላይ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ መውሰድ ፓርቲውን ያጠናክረዋል።
  • ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው የለየለት እርምጃ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እንዲወስድ ሰበብ መፍጠር ይሆናል።ባስ ሲልም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል።
 4. በተመሳሳይ ሁኔታ “ኢህአዴግ እርስ በርሱ ቢጫረስ ደስታችን ነው ያፈነገጡትን የራሳችሁ ጉዳይ ማለት ተገቢ ነው” ለሚሉ ተስፋ ከቆረጡ ሰዎች የሚሰነዘሩ ወልጋዳ ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ሲቻል;
  • ባሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ እርስ በርሱ እንዲከፋፈል እንዲጋጭና እንዲባላ እንፈልግ ይሆናል። ይህ ሲባል ግን ከህዝብ ወገን የሆኑ የኢህአዴግ አንጃ መበላት የለባቸውም። ምንም እንኳን የመሸ ቢሆንም በጸጸት ለተመለሰና በቃኝ ላለ ካድሬ ህዝብ እጁን ዘርግቶ መቀበል ይኖርበታል። ካለመቀበል የተሻለ አማራጭ ነው።
 5. በመጨረሻ በማንኛውም መንገድ ህውሓት ሲዳከም ወይም ከፖለቲካ ውጭ ሲሆን አገሪቱ ሰላሟን የምታገኝ መሆኗን በመገንዘብ በተቻለ መጠን የአጋር ድርጅቶች ከህዝብ ወገን እንዲሆኑ የተለያዩ ቅስቀሳዎችንና ሎቢ የማድረግ ስራዎችን ማፋጠን በጣም አስፈላጊ ነው።
  • ይሄኛው ነጥብ ለተቃዋሚዎች የማይጥም ጥሪ ሊመስል ቢችልም አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ለመታደግ የሚያስችል ምናልባትም ብቸኛው መንገድ ሊሆን ይችላል። ለአጋር ድርጅቶቹ ህልውና ዋስትና ሰጥቶ ከህዝብ ጎን ማሰለፍ ከተቻለ ቢያንስ እንደዜጋ የሰላም አየር እንተነፍሳለን። ካልሆነ ግን ህውሃት በበላይነት ከሚመራው ፓርቲ ስር ሆነው ህልውናቸውን ማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ያገኙትና ህውሓት ለሚወስዳቸው ማንኛውም እርምጃዎች ድጋፋቸውን ሊገልጹ ይገደዳሉ።

ዞሮ ዞሮ የህዝብ ትግል ያሸንፋል። በአነስተኛ የህይወትና የንብረት ኪሳራ ድል ለመቀዳጀት ግን ጥንቃቄ የተሞላበት የትግል ስልት ያስፈልጋል። ከህዝቡ ወገን ለሚቆሙ አንጃዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ድርጅቱን አዳክሞ በህዝብና በአገር ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን መቀነስ ስለሚችል ትኩረት የሚፈልግ አማራጭ ሆኖ አገኘሁት። ምን ትላላችሁ?

 

1 reply
 1. ዳዊት
  ዳዊት says:

  ሰላም ***

  በመጀመሪያ በአገራችን ህዝብ ላይ አሸባሪው ህወሀት እየፈጸመ ባለው ጭፍጨፋ በጣም አዝናለሁ ብርታቱን ለሁላችን አገር ወዳድ ዜጎች እንዲሰጠንም እለምናለሁ። ጥሩ እይታና ማብራሪያ ነው ያስቀመጥሽው። እኔ ወያኔ ማጣፊያው ሲያጥረው ምን ሊያደርግ ይችላል? እኛስ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፍን አገር ወዳዶች የምንፈራው እንዳየመጣ ምን ማድረግ አለብን ብዬ ሳስብ የሚከተለው ነው የመጣልኝ። ካንቺ ሀሳብ ጋር በተወሰነ መልኩ የሚመሳሰል እይታም አለኝ
  ወያኔ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ጥያቄ ነው በቅጡ መመለስ ያለብን
  በመጀመሪያ ወያኔ እንዴት እስካሁን ስልጣን ላይ መቆየት ቻለ የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል። ሁለቱን ትልልቅ ህዝቦች ጠላታሞች አድርጓቸው፤ እነሱም ጠላታሞች ናችሁ ሲባሉ አሜን ብለው ተቀብለው ወያኔ ያለምንም ሀሳብ ስልጣኑን በማናለብኝነት አንቆ ይዞ መቀመጥ ችሏል። ስለዚህ ይሄንን ስልጣን ላይ ያለገደብ እንዲቀመጥ ያስቻለውን ነገር መስበር የመጀመሪያው ስራችን መሆን አለበት።
  – በአማራና በኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ትብብር ማድረግና የጋራ የሆነ መሰረት መጣል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ዴሞክራሲ ሀይል ያደረጉትን ትብብር ሌሎቹም የኦሮሞ ድርጅቶችና የአማራ ድርጅቶች ማድረግ አለባቸው። ወያኔ እንደ ህጻን ልጅ ለ25 ወይም 40 ዓመታት ሲያታልለን (አጼ ሚኒልክ ጡት ቆረጡ፣ ስንት ሚሊዮን ኦሮሞዎች ገደሉ ማናምን ሲባል የነበረው የወያኔ ድርሰት ሙሉ በሙሉ ልብ ወለድ መሆኑ ታውቆ ዋናው ጠላታችን አሸባሪው ወያኔ ለምን ይህን ያህል ደረጃ ሄዶ ሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች ለማጋጨት እንዳስፈለገው ተረድተን ተረታቸውን ተረት መሆኑን አውቀን ወደፊት መጓዝ አለብን።) ወያኔ እነዚህን ህዝቦች ለማጣላት ሌሎች ወጥመዶች ይኖሩታል። ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ማንኛውንም የከፋ ነገር መጠቀሙ አይቀሬ ነው። ስለዚህ ሊመጣ የሚችለውን መጥፎ ነገር ለመቀነስ እነዚህ ሁለት ብሄረሰቦች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው።
  ሌላው የምራቡን አለም ድጋፍ ለማግኘት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ያስፈልጋል። የምእራቡ አገራት በአገራችን ፖለቲካ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉትን በተናጠል ማነጋገርና ማማከር ዕንዲሁም ድጋፍ መስጠት በጣም ይከብዳቸዋል። ምክንያቱም ከአንድ ደርዘን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ውርውር እያሉ ስንቱን ጠርተው ያነጋግሩ? ስንቱንስ ያማክሩ? ለምንድን ነው በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ መሪዎች መተባበር ያቃታቸው? ለምንድን ነው የሀገራቸውን ጥቅም ከራሳቸው አስበልጠው የማያዩት? አንድ የአማራ ድርጅት ከኦሮሞ ድርጅት ጋር አብሮ መስራት እኮ ግዴታው ነው!
  በብሄር ስም የሚታገሉት ስልጣን ላይ ቢወጡ ሌላውን ዞር በል ሊሉት ይፈልጋሉ ማለት ነው እንዴ? ያ በፍጹም የሚቻል ነገር አይደለም! እንደዛ እያሰበ ያለ ካለ ከተኛበት አልነቃም ማለት ነው። ከዚህ ቦሃላ እዛች አገር ላይ አንድ ብሄር ብቻ ስልጣን ይዞ መሟጨጭ በፍጹም አይቻልም! ማንም ይሄን አይፈቅድም! ይሄንን የሚፈቅድ ተቃዋሚ ሆኖ የሚታገል ካለ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ወያኔ እኮ ያንን ነው ያደረገው። በዛም ምክንያት ነው ከየአቅጣጫው አመጽ የተነሳበት። ያን ስላደረገ ነው ይሄ ሁሉ ንጹሀን በየቀኑ ደሙ የሚፈሰው። ያን ስላደረገ ነው ዛሬ አገራችን በሙስና ውስጥ ተዘፍቃ በድህነት የምትማቅቀው። እንጂ የአንድ ብሄር የነገሰበት ሀገር ከመመስረት ቀድሞውኑ ሁሉንም በዕኩልነት የሚያሳትፍ ሥርዓት ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ በደል አይመጣም ነበር። ታድያ አሁን አንድ በብሄር የሚታገል ድርጅት በለስ ቀንቶት ሥልጣን ላይ ቤወጣ ሌላውን ብሄር እንደማይበድልና እንደማያሳድድ ምን መያዣ አለን??
  የዚህ ጥያቄ መኖርና አለመመለስ ትግሉን ጎዶሎ ያደርገዋል። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ትግሉን እስከመጻረር ይደርሳሉ። ለወያኔም ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል፤ መተማመንን ስለሚያሳጣ የጎንዮሽ ትግል ይፍጥራል።
  ስለዚህ መሆን ያለበት ምንድን ነው፡ በብሄር የሚታገሉ ድርጅቶች የትግላቸውን ስትራቴጂ ሳይቀይሩ ለሌላው በብሄር ለሚታገል ወይንም የአንድነቱን ጎራ ተሰልፎ ለሚታገል ማስተማመኛ መስጠት አለባቸው። በአንድነቱ ጎራ የተሰለፉ ሁሉን አቀፍ ነን ብለው ስለሚንቀሳቀሱ ማስተማመኛው እንዳለ መጠበቅ ይቻላል። ይህ ማስተማመኛ የሚመጣው ተቀራርቦ በመስራት፤ በመተማመን፤ በመተባበርና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ የወደፊት ዕቅድ/Platform/ አብሮ በማውጣት ነው።
  ይህ ማስተማመኛ አሁኑኑ በትግል ላይ እያሉ ተስማምተው፣ ወያኔ ማጣፊያው ሲያጥረው በሚወስደው የሞት ሽረት እርምጃ ሊመጣ የሚችለውን እልቂት ለመቀልበስ ወይንም ቀድሞውኑ እንዳይመጣ ለማድረግና ለመከላከል ቀድሞ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህ ዝግጅት የሚጀምረው በጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጦ፣ ተወያይቶ፣ ተማምኖና ተግባብቶ ወጥ የሆነ የጋራ አቋም ወይም መሰረት በመያዝ ነው። መተማመኑ ከመጣ በኋላ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣትና ወደህዝቡ እንዲደርሱ በማድረግ ህዝቡና መሪዎቹ ተመሳሳይ ጀልባ እንዲቀዝፉ ማድረግ ይቻላል።
  ይህንን ከትግሉ ጋር ጎን ለጎን በማድረግ ወያኔ ያንን የፈራነውን እልቂት ሊያመጣ የሚችለውን ካርድ በሚመዝበት ግዜ ህዝቡም መሪዎቹም ቀድሞ የተዘጋጁበት ስለሆነ እንደ ከዚህ በፊቱ በተቀደደላቸው ቦይ አይፈሱም፤ ግራ አይጋቡም፤ አይጠላለፉም ትግላቸውን በተቀናጀ መልኩ ማካሄድ ይችላሉ። የፈራነውን እልቂት ማስወገድ ወይንም መቀነስ ከመቻላችን በላይ ወያኔን ወደመቃብሩ በፍጥነት ለመሸኘት ይቻለናል።
  ወያኔ ወድቆ መንግስት በሚለወጥበት ወቅትም እነዚህ ቀድሞውኑ በጋራ ለመስራት የተስማሙት ድርጅቶችና ህዝቦች ቀድሞውኑ በጣሉት መሰረት/ዕቅድ/Platform/ አማካኝነት ተማምነው ከሌሎችም የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ሰዎች/ቡድኖች ጋር በጋራ በመሆን ለሁሉም ህዝቦች እኩል የሆነና ምንም አይነት አድልዖ የሌለበት ስርዓት መፍጠር ይችላሉ።

  ወያኔን ባስተሳሰብ መብለጥ አለብን። ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ቀድመን ተረድተን ለዛ የሚሆን አጸፋዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን። ልክ አንቺ እንደዘረዘርሽው ሊያደርግ የሚችላቸውን አማራጮች ቡሙሉ በማጤን ቅድመ ዝግጅት ማድረግና መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ከተባበርን እነዚህን የአገር ነቀርሳዎች ለማስወገድ ቀላል ነው።

  ሁላችንም መስራት ያለብን ለሁላችንም የምትሆን፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ ከዘረኝነት የጸዳች፣ ሁሉንም ዜጎች በዕኩል አይን የምታይ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ነው እንጂ አንዱን ዘረኛ አምባገነን አውርደን ሌላውን ዘረኛ አምባገነን ወደስልጣን ማውጣት አይደለም!!! ይህም ከእግዚያብሔር ጋር ይቻላል።
  እንዴት ታዩታላችሁ?
  ዳዊት

  Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *