ቄሮ ፓወር (Qeerroo Power) ?

ሰለሞን ነጋሽ 

ለውጥ የመጣው በቄሮ ጉልበት ይመስላቸውና አንዳንዶች አቅማቸውን ባለማወቅ ይታበያሉ። እርግጥ ነው ቄሮ ማገዶ ሲሆን፣ ሌላውን ሲማግድ፣ እርስ በእርሱ ሲፋጅም አይተናል። ክፉና ደጉን መለየት የማይችል፣ ለነውጥ ቅርብ መሆኑን ያሳያል። በስሜት እየተነዳ ይከተላል እንጂ መድረሻ ግብ የለውም። ይህም ይመስለኛል ለነውጥ ቅርብ ያደረገው።

ለውጥ በትክክል የመጣው እንዴት ነው?

1. ከመለስ ሞት ብኋላ የስልጣን ክፍተት ተፈጠረ። ያ ክፍተት የውስጥ ሹክቻን ፈጠረ። ሽኩቻውን ለማሸነፍ የህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የሚያምኑ ህዝብን አሳመጹት። ለምሳሌ ኦሮሚያ አመጽ የተጀመረው፣ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሰበብ ነው። ያን ማስተር ፕላን ቁልፍ የፖለቲካ አጀንዳ ያደረጉት ኦህዴዶች ናቸው። OMN አይደል፣ ኦነግ አይደል፣ ቄሮ አይደል፣ ምንትሴ አይደል፣ ኦህዴድና ኦህዴድ ብቻ ነው። ያ ማስተር ፕላን ኦህዴድ ከተላላኪነት ወጥቶ የራሱን ቁመና ለመፍጠር የሞከረበት፣ የውስጥ አንድነቱን ለማጠንከር የተጠቀመበት ነበር። በወቅቱ ወያኔ ቶሎ እጃቸውን እንዳይቆርጥ፣ በየስብሰባው የሚነገረውን ዛቻና ድንፋታ፣ በሚስጥር ቀርጸው ለሚድያ በመበተን፣ ህዝብ ከጎናቸው እንዲቆም አድርገዋል። ሚድያዎች ሲያራግቡትና ካድሬዎች ውስጥ ለውስጥ ሲሰሩበት ህዝብ ለአመጽ ተነስቷል። OMN መረጃ በኦሮምኛ የማቀበል ሚና ብቻ ነው የነበራት። አስታውሳለሁ እነ ጀዋር በSBS ቀርበው መሪ የሌለው ህዝባዊ አመጽ ነው፣ የኦሮሞ አባቶች ናቸው ስርዓት እያስያዙት ያሉት፣ ሲሉ። ያን ግዜ የኦነግ መሪ ከኤርትራ በኢሳት ቀርቦ የአመጹ መሪ እኛ ነን አለ። ክሬዲት በአቋራጭ መሻማት ሲጀምሩ፣ እነ ጀዋር ቶሎ ከርበት ብለው በተጠና ስትራቴጂ ንቅናቄውን የመራነው እኛ ነን ብለው ክሬዲቱ ለመውሰድ ሞከሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ዋናው አክተር (ኦህዴድ)እኔ ነኝ ማለት አይችልም ነበር፣ በወያኔ ጅብ እንደሚበላ ያውቃታላ!የሆኖ ሆኖ ወደ መጨረሻ አካባቢ ከብዙ የፕሮፓጋንዳ ስራና በኦህዴድ ይሁንታ OMN ላይ ያሉ አክቲቭስቶች የትግሉ መሪ መስለው ብቅ አሉ። OMNን መረጃ የሚያቀብለው፣ እቅድ የሚሰጠው፣ አንዳንዴ መግለጫ መሳይ ነገር የሚሰጠው ኦህዴድ ውስጥ የነበረ የለውጥ ሀይል ነበር። OMNኦች ኦህዴድን የተጠቀሙበት ይመስላቸዋል። እውነታው ግን ኦህዴድ ነበር OMNን የተጠቀመበት።

ኦህዴድ ዛሬ ስልጣን ይዟል። ስልጣን ይዞ ለአገር ይበጃል ብሎ የሚያምንበትን ለውጥ በብርሀን ፍጥነት እያከናወነ ይገኛል። OMN አሁንም ከሳተላይት አልወረደችም። አሁንም ስሜት እየኮረኮረች ቄሮን ለማስጮኽ ትሞክራለች። ኩርፊያው ባልከፋ፣ ተፈጥሯዊ ነውና (እነ ህዝቄል የአማራ መንግስት ነው የመጣብን እኮ ብለው ሲያለቃቅሱ ሰምቷችኋል መቼስ)። ችግራቸው አቅማቸውን አለማወቅ፣ ለራሳቸው የሚሰጡት ሰልፍኢሜጅ እንደ ወደቁት ወያኔዎችና በአጭሩ ተኮላሽቶ እንደቀረው ዳውድ ኢብሳ የተጋነነ መሆኑ ነው። ቄሮን ለአመጽ በመጥራት አይደለም፣ በማስታጠቅና ዝርፍያና ግድያ ውስጥ በመክተትም፣ ያሰብነውን ማሳካት እንችላለን ብሎ የተነሳም ነበር። ተኮላሽቶ ቀረ፣ ሸምግሉኝ ብሎ አለቃቀሰ፣ እንጂ የትም አልደረሰም። እና አቅማችሁን ብታውቁ ጥሩ ነው። ታሪካችሁንም መለስ ብላችሁ ብትመለከቱ ጥሩ ነው። የድሮውን ተዉትና በአንድ አመት ውስጥ የሆነውን ልብ ብላችሁ መርምሩ፣ ኦሮሞ ከሶማሌ፣ ከደቡብ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከአማራ፣ ከሀረር፣ በቡራዩ ከጋሞ፣ ከትግሬ ጋር ተላትሟል። ሺዎችን አፈናቅሏል። በሺዎች የሚቆጠር ተፈናቅሏል። ይህ ብቻ አይደለም፣ ጅማ ኦሮሞና የወለጋ ኦሮሞ እየተባባለ እርስ በእርሱ ፍጥጫ ውስጥ ነው። በሽፍታ ኦሮሞና መንግስቱን በሚመራው ኦሮሞ ስም ንጹሀን የእሳት እራት ሆነዋል። የአገር ንብረት ወድሟል። በስልጣን ጥመኛ ኦሮሞና መንግስቱን በሚመራው ኦሮሞ መካከልም ሌላ ፍጥጫ አለ። በግጭት ላይ ግጭት እንደገና ሌላ ግጭት እያስተናገደ ነበር ኦሮሞ አመቱን የፈጀው። አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ ጋር ሊያፋጁት እያኮበኮቡ ነው። ቆይ ግን እንደምትጎረሩት አዋቂ ከሆናችሁ፣ የሰውና የተፈጥሮ ሀብት ካላችሁ፣ ወለጋን እንደ አዲስ አበባ ማሳደግ አይቻልም እንዴ? ምንድን ነው ሶስት ትውልድ ላቡን አንጠፍጥፎ ያቀናውን ከተማ ለመዝረፍ መቋመጥ? ባንክ እንደመስበር ቀላል እንዳይመስልህ! ዋ!

2. የነበረውን ግጭትና ግጭቱን ለመፍታት የተጠቀሙበት አካሔድ ስህተት ስለነበር፣ ሀይለማርያም ደሳለኝ ቀርቶ የአባዱላ ህሊናም ሊቀበለው ስላልቻለ፣ ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል ተፈጥሮ፣ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የተገደዱ መሪዎች ነበር። የነአባዱላና ሀማደ መልቀቂያ፣ በድርጅቱ ለስነልቦናዊ ጫና ከመፍጠሩም በላይ፣ አዲስ መሪ እንዲመጣ በር ከፈተ። ሀይላማርያም ቆዳውን የዝሆን ቆዳ አድርጎ ግድ ሳይሰጠው ስልጣን ላይ ሙጭጭ ቢል ኖሮ ቄሮ ዛሬም ድረስ ድንጋይ ከመወርወር፣ እስር ቤት ከመማገድና በጥይት ከመቆላት አያልፍም ነበር። የሀማደ መልቀቅ ቁልፍ ነበር። እውቅና መስጠት አይሆንልንም እንጂ!

3. .የሀማደን ቦታ እንደምንም ተሟሙቶ በተቀናጀና በበሳል ስትራቴጂ ለማ ገዱን አሳምኖ፣ ሁለቱን ድርጅቶች አግባብቶ፣ አብይ እንዲመረጥ አደረገ። አብይ እንዲመረጥ የለማና የገዱ ብቻ አይደለም የደመቀ አስተዋጽኦም ትልቅ ነበር። እነዚህ ሰዎች ባይኖሩ፣ ኖረውም ያንን ስልት ባይከተሉ፣ ዛሬ ለውጥ ባልመጣ ነበር። ምናልባት ሽጉጤ ቦታውን ይዞ ደም ሲያስተፋይ ይኖር ነበር። ለነዚህ ሰዎችም በትልቁ እውቅና መስጠትና ማመስገን ይገባል።

4. ህወሓት ራሱ እጅግ የምትመሰገንበትን አስተዋጽኦ አበርክታለች። ወዳም ይሁን ተገዳ፣ በድርጅቷ ውስጥ የተፈጠረውንና ገፍቶ የመጣውን ለውጥ በድምጽ ብልጫ ተሸንፋ፣ መሸነፏን አምና በጸጋ ተቀብላ አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኗል። እንደመለስ ዓይነት ፖለቲከኛ ቢኖራት ኖሮ ይህ የማይታሰብ ነው። አስታውሳለሁ ዳንኤል ብርሀነ እንኳን በአቅሙ ሽንፈታቸውን እንዳይቀበሉ የተለያዩ ስልቶችን ሲያቀርብ። ፓርላማው ይፍረስ ከማለት አንስቶ አብይንና ለማን ለማሰር ኬዝ እስከመፍጠር ድረስ ሙከራ አድርጓል። ህወሓት የዚህን ዓይነት የጥፋት ምክር ተቀብላ ተግባራዊ ሳታደርግ ውጤቱን መቀበሏ ያስመሰግናታል። ለለውጥ በሯን እንደከፈተች ይቆጠራል። ምንም እንኳን ከገመተችው በላይ ጥቅሟን የነካ ለውጥ ሆኖ ኋላ ለኩርፊያና ለእንቅፋትነት ቢዳርጋትም፣ መጀመሪያ የአብይን ሊቀመንበርነት መቀበሏ በታሪኳና በታሪካችን ቁልፍ እርምጃ ነበር።

5. በመጨረሻም ለውጡ የኢንጅነሮቹ ስራ ነው። አብይ እዛ ቦታ ባይሆን፣ ከአብይ በስተጀርባ እነለማና ደመቀ እንዲህውም የእኔ ዓይነት አክቲቪስት ሃሃ ባይኖር ኖሮ፣ ይህ ዛሬ የምናየው ለውጥ የማይታሰብ ነበር። ህዝባዊ ድጋፍን የሚያስገኝ የለውጥ ጅምር ነበር። ጥቂት ያኮረፉ ዘውጌዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ ያመነበትና የረካበት የለውጥ ጅምር ነው። ይህን የለውጥ ጅምር አንዴ ባንክ እየዘረፍክ፣ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባን የፖለቲካካርድ እያደረክ፣ መንጋህን አሰባስበህ ልታደናቅፈው አይቻልህም። ባለፈው ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ሲወያዩ ሳይ ለውጡ በትክክል የህዝብ ለውጥ እየሆነ ለመምጣቱ አምኛለሁ። እና እነ ጀለስካ ለውጡ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ እየሞላ ነውና እየየውን ትታችሁ ቶሎ ተሳፈሩ!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *