አማራና የአማራ ብሔርተኝነት

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃዋሚ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ብዙ ማነቆዎች እንዳሉ ይታወቃል። ጠንከር ያለው ማነቆ የኢኮኖሚ አቅም ይመስለኛል። የፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ በቂ የኢኮኖሚ አቅም የላቸውም። አብዛኛው የገቢ ምንጫቸው ከአባላት የሚገኝ ገንዘብ ነው። ይህ ደግሞ ከአባላቱ ቁጥር ማነስ ጋር ወይም ከዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅማቸው ጋር ተያይዞ አነስተኛ ነው። ስለሆነም አብዛኛውን ጊዜ ከውጭ “ለጋሾች” ድጋፍ ይጠይቃሉ። ከውጭ ድጋፍ ለማግኘት፣ “በለጋሾቹ” ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርክት/አጀንዳ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። “በለጋሾቹ” ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርክት ደግሞ የማታ ማታ የለጋሾቹን ጥቅም የሚያስጠብቅ ትርክት ብቻ ነው። ታዋቂው ኢኮኖሚስት ሚልተን ፍሪድማን እንዳለው “There’s no such thing as a free lunch.”

አማራ እና የአማራ ብሔርተኝነትለዚህም ነው ከአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በቁጥር ተቀራራቢ የሆኑ የብሔር ፖለቲካ የሚያቀነቅኑና ህብረብሔራዊ አንድነትን የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢቋቋሙም፣ ለረዥም ጊዜ መቆየት የቻሉትና የፖለቲካ ባህላችንን መቅረጽ የቻሉት እንዲውም ለስልጣን የበቁት፥ እስከመገንጠል ድረስ አጀንዳ ይዘው የተነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሆኑ የቻሉት። እነ ኢህአፓ፣ መኢሶንና ኢዲዩ፣ በወያኔ ሻዕቢያና ኦነግ ተበልጠዋል። እንዲህውም በኛ ትውልድ በአንድነት ከተደራጁት ይልቅ በብሔርተኝነት የተደራጁት የተሻለ አቅም ሲያካብቱ እያየን ነው። ከዚህ አንጻር ስናየው የአገራችን ፖለቲካ ባመዛኙ የተቃኘው በውጭ ለጋሾች ድጋፍና ፍላጎት ነው ማለት ይቻላል።

ለእነዚህ የዘውግ ፖለቲከኞች በውጭ ለጋሾች ዘንድ ሰፊ ድጋፍ ያስገኘላቸው ትርክት፥ በአማራ የበላይነት መጨቆናቸውን የሚተርክ ትርክት እንደሆነ ይታወቃል። ህወሓት የታገለው የአማራ ታሪካዊ ጠላትነት ትርክትን በታጋዮቹ ላይ እያሰረጸ ነበር። ሻዕቢያ የታገለው በአማራ የበላይነት በሚመራ መንግስት ቅኝ የመገዛት ትርክትን እያነበነበ ነበር። ኦነግ የታገለው በአማራ የበላይነትና ጨቋኝ ብሔርተኝነት ቅኝ የመገዛትና የመገለል ትርክት እያቀነቀነ ነበር። እነዚህ ትርክቶች ከፍተኛ የውጪ ድጋፍ ከማስገኘታቸውም በላይ፥ የኔ የሚሉትን “ብሄር” ለማንቀሳቀስ ረድቷቸዋል። ወያኔና ሻዕቢያን ደግሞ ለስልጣን አብቅቷቸዋል።

በድግግሞሽ ብዛት እውነት የመሰለ ትርክት

የአማራ ምሁራን ሳይቀር የሚያደንቋቸው እነ ዶናልድ ሌቪን፣ በጥናታዊ ስራዎቻቸው የሚያስተጋቡት ነገር ቢኖር፣ ባለፉት መቶ ምናምን አመታት የአማራ የበላይነት እንደነበረ ነው። ይሁን እንጂ “ይህ የበላይነት በምንና እንዴት ይገለጻል?” የሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ የተገኘለት ጥያቄ አልነበረም። ነገር ግን በድግግሞሽ ብዛት ያለተጠየቅ በብዙዎች ዘንድ ቅቡል የሆነ ትርክት ነው። እስከዛሬ ድረስም ሲሰራበት የኖረ ትርክት ነው። ውጤቱም በአማራው ላይ የጠላትነት ስሜት ማሳደርና በቀልን መሻት ሲሆን አይተናል።

ለምሳሌ ከቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ሲዋጉ የኖሩት የወያኔ፣ የሻዕቢያና የኦነግ ታጋዮች፣ በዚህ ትርክት እይታ ሲዋጉ የኖሩት ከሁሉም ብሔር የተውጣጣ ሰራዊት ሲመራ ከነበረ የደርግ ስርዓት ጋር ሳይሆን ከአማራ ጋር ነበረ። ደርግ በወደቀ ማግስት የበቀል ካራቸውን የሳሉትም ለዚህ ነው። ሻዕቢያ ያኔ የማረካቸውን ምህረት የለሽ እርምጃ ወስዶባቸዋል። ኦነግ ጊዜና ሁኔታ በፈቀዱለት ጊዜ በበደኖና በአርባጉጉ አረመኔያዊ እርምጃ ወስዶባቸዋል። ህወሓት ይኸው እስከዛሬ ድረስ በግልጽም በህቡእም መንገድ አማራ የሚለው ህዝብ ላይ የግፍ ዱላውን እንዳነሳ አለ።

ይህ ሁሉ ሲሆን እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ተጠቂው ማህበረሰብ ሌላው ቀርቶ ራሱን እንኳን በአማራነት የማይለይ መሆኑ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ወርዶ ራሱን ካየ በቀየው ነበር ማንነቱን የሚገልጸው። አዲስ ስያሜ ሰጥተው፣ በጠላትነት ፈርጀው፣ የበቀል መወጣጫ ሲያደርጉት፣ ራሱን መከላከል ያልቻለውም ለዚህ ነበር። በአጭሩ ባለፈው ታሪካችን ለተከሰቱ የአስተዳደር በደሎች “አማራውን” እንደ scapegoat ተጠቅመውበታል። በማያውቀው ጉዳይ scapegoat ሲሆንና ባልተደራጀበት ሲጠቃ ዝም ብሎ ማየት ስህተት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ነው። ግራህን ሲልህ ቀኝህን ስጠው ብሎ ነገር እዚህ ላይ አይሰራም። የሚሰጥህ ጥፊ ሳይሆን ጥይት ነውና!

ይህ ግፍና በደል ነው እንግዲህ የአማራ ብሔርተኝነትን ከፈጠራ ትርክት ፈልቅቆ በተግባር እንዲወለድ ያደረገው። ትርክቶቹ ያለ እርማት በቀጠሉበት ሁኔታ እንቅስቃሴው ከተወለደ ብኋላ እንዲቀለበስ መሞከር ትክክል አይሆንም። ባለው ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ የአማራን ጥቅምና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እንዴት ከሌሎች ጋር ተቀናጅተው መስራት እንደሚኖርባቸው በግልጽ መነጋገሩ የተሻለ ይመስለኛል።

እንደተባለው በአማራነት ተደራጅተው ራሳቸውን ለመከላከል መንቀሳቀሳቸው ትክክልና ተገቢ ነው። ነገር ግን ሊስተካከሉ የሚገባቸው አካሄዶች አሉ። ከብዙ በጥቂቱ ሚዛን የሚደፉትን እንሆ፣

  1. በብሔር ተደራጅተው ሲታገሉ የቀድሞ ብሔርተኞች በተጓዙበት የጥፋት መንገድ ሳይሆን ራሳቸው በቀየሱት አዲስ የትግል ስልት ሊሆን ይገባል።
  2. በአማራነት ተደራጅተው የሚታገሉት፣ ራሳቸውን ለመከላከልና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንጂ ለበቀል መሆን የለበትም። ስለሆነም ዛሬ በጥላቻ የተለወሱና ለበቀል የሚያነሳሱ ትርክቶችን ከመፍጠር መቆጠብ ይኖርባቸዋል።
  3. ሁለት ወዶ አይሆንም። ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት አይቻልም። የጀመሩት መንገድ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የብሔርተኝነት አጀንዳቸውን ብቻ በአግባቡ ያራግቡ። ኢትዮጵያዊነትን መስበክና ማራገብ ካለባቸውም በዛ በብሔርተኝነት ማእቀፍ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት። የአማራ ብሔርተኝነትን እያራመድክ፣ ስለአንድነት መስበክ አይቻልም። ይህ ለነሱም አንድነት ለሚያራምዱትም የማይበጅ ደንቃራ እንቅፋት ነው።
  4. አንድነትን የሚያራምዱትንም ይሁን ሌሎች የብሔር ፖለቲከኞችን በጠላትነት ማየት የለባቸውም። ብዙ ጊዜ ለምንና ከማን ጋር እንደሚታገሉ ለማወቅ ግራ እስኪያጋባ ድረስ ከሁሉም ድርጅት ጋር የመላተም ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ይህን ማስተካከል ተገቢ ነው።
  5. ትግል ያለስልትና ስትራተጂ የትም አያደርስም። የሚታገሉለት ዓላማ በግልጽ ካስቀመጡ ብኋላ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው በዝርዝር ስልት ቀይሰውና ስትራተጂ ነድፈው እስካልተንቀሳቀሱ ድረስ፣ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት አያፈራም ብቻ ሳይሆን ወደ መጥፎ ሁኔታ ሊያመራ ይችላል። የብሔር ፖለቲካ በእሳት እንደመጫወት ነው። በጥንቃቄ ከተጠቀምክበት ብዙ ነገሮችን ቅርጽ ለማስያዝ ትጠቀምበታለህ። እሳቱ ከእጅህ ከወጣ ግን አንተንም ጨምሮ ይለበልብሃል። እናም ከሁሉም ጋር የሚያላትምና ስነምግባር የጎደለው የዛሬው ያልተገራ አካሄድ ይታረም ዘንድ ስልትና ስትራተጂ መቀየስ ግድ ይላል።
  6. በአማራ ብሔርተኝነት የተሰባሰቡ በርካታ ድርጅቶች አሉ። አንዳንዶቹ በጎንዮሽ ግጭትም የተጠመዱ ናቸው። በትክክል ለአማራ የቆሙ ወደ አንድ ወይም ሁለት ድርጅት መሰባሰብ ይኖርባቸዋል። በአማራ ህዝብ ስም የሚነግዱና ውዥንብር ለመፍጠር የተሰማሩ በግልጽ ሊታወቁና ሊገለሉ ይገባል።
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *
RSS Solomon Negash