ንጉሳዊ፣ ወታደራዊ እና አጭቤ አምባገነኖችን አይተናል፤ ፖፕሊስት አምባገነንስ?

ቃዛው የዓለም ጦርነት ሲገባደድ አካባቢ ፍራንሲስ ፉክያማ The End of History የተሰኘውን መጽሀፉ ለንባብ አበቃ። ፖለቲካል ትዬሪስትና ፖለቲካል ፊሎሰፈርስ ከነሶቅራጠስ አንስቶ ዘመናቸውን የሚገልጹ ፈላስፋዎችንና ስራዎቻቸውን ሲጠቅሱ ይህን የፉክያማ መጽሀፍ ከኛ ዘመን ይጠቅሱታል። ፉክያማ በዚህ መጽሀፉ የሚከራከረው የሰው ልጅ የመጨረሻው ግቡ ሊበራል ዴሞክራሲ ነው ብሎ ነው። ‘አሁን እዛ ግብ ላይ ደርሰናል፣ የሚቀረው ሁሉንም ማዳረስ ነው። ይህን ርዕዮተ ዓለም የሚያሸንፍና ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል ሌላ የተሻለ ርእዮተ ዓለም የለም’ ከማለት አልፎ ሊፈጠር አይችልም ብሎም ይከራከራል። መጽሀፉ በቀዝቃዛው ጦርነት የተጋጋለ ስሜት ውስጥ ሆኖ የተጻፈ ስለነበረ አሜሪካ ለምትከተለው ርእዮተ ዓለም ማዳላቱ የሚገርም አልነበረም። ትችቶች ወዲያ ተሰንዝረውበታል።

 ዋነኛው ትችት የተሰነዘረበት ከራሱ አስተማሪ ከSamuel Huntington ነበር። The Clash of Civilisation በሚለው መጽሀፉ Huntington ለማንነት ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ በመስጠት የፉክያማን ክርክር ይንደዋል። የፉክያማ ቴሲስ ትኩረት ያደረገው ዓለምንና ዘመናትን የሚገዛ አውራ ርእዮተ ዓለምና ስልጣኔ ነበር። ሀንቲግተን ግሎባል የሚባል ስልጣኔና አውራ የሚባል ርዕዮተ ዓለም ሊኖር አይችልም። ከህዝብ ብዛትና ከንቃተ ህሊና ማደግ ጋር ተያይዞ መጪው ዘመን የሚቃኘው መሰረቱን ሎካል ባደረገ የማንነትና የባህል ፖለቲካ ወይም ርእዮተ ዓለሞች ነው ይላል። ለዚህም ነው የስልጣኔዎች ግጭት ይኖራል ለማለት The Clash of Civilisation የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ያቀረበውና የመጽሀፉን ርዕስ ያደረገው። 

ሀንቲግተን እንደተነበየው ዛሬ በማንነትና በባህል የሚቃኝ ፖለቲካ አለምን እየቀረጻት ይገኛል። የቻይናና የራሽያ ማንሰራራት የጠንካራ አገራዊ ብሔርተኝነት (Identity Politics) ውጤት ነው።  የISISና መሰል ኢስላሚክ ፋንዳሜንታሊስቶች እንቅስቃሴ  Huntington እንደተነበየው የማንነት ፖለቲካ ውጤት ነው። በቅርብ ግዜ ደግሞ እየገነነ ለመምጣቱና አለምን ብርድ ብርድ ለማሰኘቱ የትራምፕ መመረጥ፣ የBrexit ህዝበ ውሳኔ፣ በስካንዲኔቪያን አገራት የኒዮናዚ ቡድን አቀንቃኞች ማንሰራራታቸው፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

 በቅርቡ ፉክያማ ባሳተመው Identity በተሰኘው መጽሀፉ ቀደም ሲል የጻፈው መጽሀፍ በደንብ ያልበሰለ እንደነበር ጠቅሶ፣ አመለካከቱ በተወሰነ ደረጃ የተቀየረና ትክክለኛውን አመለካከት ስለ Political Order በሚያትቱ ሁለት ተከታታይ መጻህፍቶቹ ማስፈሩን ጠቅሶ፣ እንደተነበየው ሊበራል ዴሞክራሲ እያንሰራራ ሳይሆን የማንነት ፖለቲካ እየገነነ መምጣቱን አምኗል። የማንነት ፖለቲካ ተገን አድርገው አምባገነኖች በፖፕሊስት አካሔድ ማንሰራራታቸውንም ተመልክቷል። እንዲያውም ፋሽን እየሆነ ለመምጣቱ የአሜሪካውን ትራምፕ፣ የራሽያውን ፑቲን፣  የቱርኩን ኤርዶጋን፣ የሀንጋሪውን ኦርባን፣ የፖላንዱን ካቸንስኪና የፊሊፒንሱን ዱቴርተ እንደምሳሌ ጠቅሷል።  ሌላው አምባገነኖች የሚወጣጡበት መሰላል መሆኑ ነው።

ዛሬ ንጉሳዊና ወታደራዊ አምባገነን በዓለም ላይ በባትሪ ተፈልገውም የሚገኙ አይመስለኝም። ከዓረብ አገራት መሪዎች ውጭ ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል ማለት ይቻላል። በይስሙላ ምርጫ እያጨናበሩ ስልጣን ላይ የሙጢኝ የሚሉ Electoral authoritarianism የሚባሉ አጭቤ አምባገነኖችም እየተመናመኑ ነው። በአዲሱ የታሪክ ምእራፍ እያንሰራራ ያለው አምባገነን ፖፕሊስት  የሆነ አምባገነን ነው። አገራችን ንጉሳዊ፣ ወታደራዊና አጭቤ አምባገነኖችን አይታለች። ዛሬ ፖፕሊስት አምባገነን ሳታይ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሸጋገር የምትችልበት መስቀለኛ መንገድ  ላይ ትገኛለች። ሽግግሩ የተሳካ ይሆን ዘንድ  የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል። በተለይ ሴሌብሪቲዎች፣ ባለሀብቶች፣ የሚድያ ሰዎችና የማህበራዊ ሚድያ ጉሩዎች ታሪክ የጣለባችሁ ትልቅ ሀላፊነት አለ። ፖፕሊስት አምባገነን እንዲሳካ እናንተ ማፋጠን የምትችሉበት መንገድ በእጃችሁ ስላለ በፖለቲከኞች ትፈለጋላችሁ። ፖፕሊስት አምባገነን ተጨናግፎ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን የሚያስችል በታሪክ አጋጣሚ የተሰጠ ጸጋም እናንተ ዘንድ አለና በህዝብ ዘንድ ትፈለጋላችሁ።  ታሪክ ከየትኛው ወገን ቆማችሁ እንዲያስታውሳችሁ እንደምትፈልጉ መምረጥ ያለባችሁ ግዜ ላይ ናችሁ።    ይቅናችሁ! 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *