ለውጡ እንዳይቀለበስ ምን ላይ ትኩረት ይደረግ?

አንድ ኢንግሊዛዊ አስማተኛ (illusionist) አለ፣ የብሔራዊ ሎተሪ አሸናፊ እጣ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ “ማወቅ” የሚችል። አንድ ግዜ የሆነ ቲቪ ሾው ላይ ተመልካቹን በላይቭ አሳይቶ አስደምሟል። አሸናፊው በቲቪ ሲገለጽ አብረው ላይቭ ካዩ ብኋላ ሰውዬው ቀድሞ ያዘጋጀውን ቁጥር ያሳያል። ተመሳሳይ ነበር። እንደ ሰውዬው ገለጻ ከሆነ ሎተሪ እንዳይቆርጥ በህግ ተከልክሏል። እንዴት ቀድመህ ልታውቅ ቻልክ የሚል ጥያቄ ሲጎርፍለት ከዚህ ሳይኮሎጂና ስታትስቲክስ ላይ መሰረት ያደረገ ሳይንቲፊክ ምላሽ ይሰጣል።

The Wisdom of Crowds የሚባል ኮንሰፕት ከሳይኮሎጂ በመጥቀስ እንዲህውም The Law of Large Numbers የሚባል የሒሳብ/ስታትስቲክስ ህግ ላይ በመመስረት፣ ሎተሪው ከመውጣቱ በፊት ቀደም ብሎ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ተከታታዮቹ መጠይቅ ያዘጋጃልና poll ይሰበስባል። የዛሬው አሸናፊ የሎተሪ ቁጥር የመጀመሪያው አሀዝ ምን ሊሆን ይችላል ገምቱ። ሁለተኛው አሀዝስ? ሶስተኛው አሀዝስ? … የመጨረሻው አሀዝስ? ይህን መረጃ ከሰበሰበ ብኋላ የእያንዳንዳቸውን አቨሬጅ ወስዶ (ደሲማሎችን አጠጋግቶ) ሙሉ ቁጥሮችን በቅደም ተከተል አስቀመጠ። ያ ቁጥር አሸናፊ ሆኖ ወጣ። ለዚህም ነው የአለማችን ቀጣዩ ቁልፍ ቢዝነስ Big Data ነው የምንባለው። ለዚህም ነው እያንዳንዷን ክሊክ እንደመረጃ የሚሰበስቡት፣ እነ ጉግል አፕልና ማይክሮሶፍት እያንዳንዷን deviceና account ሲንክሮናይዝ የሚያደርጉት። ከኔ ብቻ የሚሰበስቡት በጊጋባይቶች የሚተመን መረጃ፣ ነገ ጧት ስንት ሰዓት ላይ ቡና እንደሚያምረኝ፣ ባማረኝ ሰዓት መግዛት ስለመቻል አለመቻሌ፣ ፕሪዲክት ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው። እንደዚህውም የአዲስ አበባ ኖሪዎች ፍላጎት መገመት ብቻ ሳይሆን አዲስ ፍላጎት እንዲኖራቸው እንዴት ማድረግ እንደሚቻልም ማወቅ ይችላሉ። The moral of the story is “ከብዙ ሰዎች የሚገኝ መረጃ ወይም ከአንድ ሰው በብዛት የሚገኝ መረጃ  ስለነዛ ሰዎች ለማወቅ የሚረዳና ወደ ጥቅም ሊቀየር ትልቅ ሀብት ነው!” ለማለት ነው።

እኛ የማይክሮሶፍት ወይም የአፕል ወይም የጉግል ኢንጅነሮች አይደለንም። የቢዝነስ ሰዎችም አይደለንም። ነገር ግን እንዴት የዚህ ዓይነት መረጃ መሰብሰብና ህይወታችንን መቀየር በሚችል መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንችላለን?አጭሩ መልስ – ”ዴሞክራሲን እውን በማድረግ!“  የሚል ይሆናል። ለመዳሰስ የፈለግኩት ዋናው ነጥብ ይህ ነውና ልበትነው።

ከመቶ ሚልዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት አገር እንኖራለን። ከዚህ ውስጥ 30 ሚልዮኑ በአገሩ ጉዳይ ላይ የሚሳተፍ (በምርጫ የሚሳተፍ፣ አስተያየቱን በጽሁፍ፣ በንግግርና በጥበብ የሚገልጽ፣ የሚሰበሰብ፣ ተደራጅቶ የሚታገል ወዘተ ) አክቲቭ ዜጋ ቢሆንና ይህንን አሴት ብንጠቀምበት ለዚች አገር የሚበጅ ፖሊሲ፣ ህግ፣ ህገመንግስት፣ አቅጣጫ፣ ወዘተ Perfectly ማወቅና መቀየስ እንችላለን ማለት ነው። የቁጥር ብዛት ማተር ያደርጋል። ይህ ማለት የተሻለ ነገ እንዲኖረን ከፈለግን አክቲቭ የሆነው ዜጋ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ማሳተፍ የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ ቀዳሚ ትኩረታችን ሊሆን ይገባል ማለት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ወዘተ በአሁኑ ሰዓት ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ የሚገባቸው:- እንዴት ዜጎችን ማሳተፍ ይቻላል? ሲሳተፉስ መረጃውን እንዴት መሰብሰብ ይቻላል? መረጃው ከተሰበሰበ ብኋላስ የአገሪቱን ፖሊሲና ህግን በሚቀርጽ መልኩ እንዴት ጥቅም ላይ መዋል ይቻላል? ወዘተ ለሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ በማስቀመጥ ነው። በዋናነት ሃላፊነታቸው ይህ መሰለኝ። ምክንያቱም አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያስፈልገን፣ የተሻለ አማራጭ ሀሳብ ለማፍለቅ፣ የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግ፣ ተሳትፎና ድምጻቸው ተደማጭነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ inclusive የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት የሚያስችል ቁመና ለመፍጠር፣ ወዘተ ነው። ፖለቲካል ሳይንቲስቶች (ለምሳሌ ብዙዎቻችን ባነበብነው Why Nations Fail) ሲገልጹ የምንሰማው፣ አሳታፊ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ካልተገነቡ፣ እድገትና ለውጥ ሊኖር አይችልም። ቢኖርም ዘላቂነት የሌለው ጊዜያዊና የታይታ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ሲታይ የሽግግር ወቅት ላይ እንደመሆናችን መጠን፣ ግዜው የሚጠይቀው እነዚህን ተቋማት ለመገንባት መሰረት ማኖርን ነው።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ፣ ዋና ጉዳያቸውን ትተው የትረስት ፈንድ በማሰባሰብ የተጠመዱ “አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች” ናቸው። ዛሬ አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። በመፍረስና በማዝገም መካከል ላይ የምትገኝ አገር ነች። መዋጮ መሰብሰቡን ሌሎች ይሰሩታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ካመነበት በአንዲት ጀምበር በመቶሺዎች የሚቆጠር ዶላር በጎፈንድሚ  በአንድ ሰው አካውንት  ብቻ ሲያወጣ አይተናል፣ ለምሳሌ ለአትሌት ፈይሳ!ቢሳካ እንኳን ያን ያክል ፋይዳ በሌለው ጉዳይ ላይ ግዜና ጉልበት ማባከን አያስፈልግም። ይህ ለኢህአዴግና ለዶ/ር አብይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይረዳ ይሆናል፣ መሰረታዊ የአገሪቱን ችግር ሊቀርፍ የሚችል አጀንዳ ግን አይደለም።

ዳያስፖራ በመዋጮ ከሚሰጠው መቶ እጥፍ በላይ፣ ወላጆቹን በመጦር፣ ታናናሾቹን በማስተማር፣ ጎጆ በማውጣት፣ የተቸገሩ ዘመዶቹንና ጎረቤቶቹን አልፎ አልፎ በማስታወስ፣ እንዲህውም በመኖሪያና የንግድ ህንጻ ግንባታዎች በመሳተፍ ወዘተ ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ ስራዎችን ኦልሬዲ እያከናወነ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ሲገነቡ ደግሞ ገንዘቡን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ኢንቨስት አድርጎ አገሪቱን ትራንስፎርም ማድረግ የሚችል ያልተጠቀምንበት እምቅ ሀብት ነው። የተቋማቱ ግንባታ አገሪቱን ከመፈራረስ፣ ህዝብ እርስ በእርስ ከመጫረስ ከመታደጉም በላይ ለልማት፣ ለኢንቨስትመንት፣ ዳያስፖራውንና ሌሎች በተፈጥሮ የተሰጡንን ጸጋዎች አሟጠን ለመጠቀምና ነገአችንን ለማሳመር ወሳኝ ናቸው። አማራጭ የፖለቲካ ሃይል ሳይዘናጋ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት እዚህ ላይና እዚህ ላይ ብቻ ይመስለኛል።

ዛሬ እንደበፊቱ ሳይሆን የሚበረታቱ አለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው መልካም ጅማሮዎች አሉ። ምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማት፣ የሚድያ ተቋማት፣ የመከላከያ ሰራዊት ወዘተ ገለልተኛ ተቋማት እንዲሆኑ የተጀመረው ነገር የሚያስመግን ነው። ነገር ግን ያላለቀና ወደ ኋላ ሊቀለብስ የሚችል ጅማሮ ነው። ከምንም በላይ አንድ ወይም ጥቂት ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ጅማሮ ነው። ያ ግለሰብ ወይም ቡድን ድንገት ከጨዋታ ውጭ ቢሆን፣ የተጀመረው ሁሉ ሊቀለበስ ምናልባትም ሊፈራርስ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው።በግለሰብና በፖለቲካ ፓርቲ የማይቃኝ፣ ሁሉንም ዜጋ የሚወክል ተቋማዊ ለውጥ ሊሆን ይገባል። ይህን እውን ለማድረግ ተግቶ መስራት የአማራጭ ፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ተቋማት እንዲህውም አክቲቭስቶችና ጋዜጠኞች የዜግነት ግዴታ ነው።

አይደለም በመዋጮ በሚገኝ ገንዘብ ፣ በዓመት አራትና አምስት ቢልዮን ዶላር እርዳታ እየሰለቀጡም ስንዝር መራመድ ያልተቻለበት አገር ላይ ነው ያለነው። እነዛው ተቋማት ባሉበት እያሉ መዋጮ መሰብሰብ ላይ መጠመድ ኮምፓሷን እንደሳተች መርከብ  መሀል ውቅያኖስ ላይ አዙሪት መቅዘፍ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ተቋማቱ አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉና ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ቢደርግ እንኳን፣ ተያይዞ ከሚመጣው efficient የሆነ ሪሶርስ አጠቃቀም፣ በ10 ዓመት በመዋጮ ሊሰበሰብ ከሚችለው በላይ በወራትና በአመት ውስጥ ማትረፍ ይቻላል። በአገር ደረጃ ቀርቶ ዋና ከተማዋ ላይ ብቻ የአሰራር ለውጦች ቢደረጉ ስንትና ስንት ሚልዮን ብር ማትረፍ ይቻላል። የቱንም ያህል ቢለፋና ቢሞከር፣  ለረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ የተመደበውን ያህል ገንዘብ እንኳን በአመት በመዋጮ መሰብሰብ አይቻልም። ያ ገንዘብ የት ገባ? አሁንስ የተለየ ተቋም የተሻለ አሰራር ነው ወይ ያለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ቅሌት ወጥታችሁ መንግስት መሆን የምትችሉበትን ቁመና መፍጠራችሁን ለህዝቡ ማሳየት ተገቢ ይሆናል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *