ከትግራይ መንግስት የተሰጠ መግለጫ – ጥር 22 2013 ዓ.ም

በትግራይ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)

(ብትግርኛ ንምስማዕ)

በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የምትገኝ የትግራይ ህዝብ፣

ክቡራን እና ክቡራት፡

አስቀድሜ ዋነኛው የወራሪዎች ምከታና ትግል ከሚካሄድበት የትግራይ ሜዳ፣ ለናንተና ለትግላችሁ ያለኝ አክብሮትና አድናቆት በመግለጽ በትግል መንፈስ ሰላምታየን አቀርባለሁ።

ክቡራን እና ክቡራት፣

የትግራይ ህዝብ ህልውናውንና መብቱን ለማስከበር፣ እንዲሁም ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በተግባር ለማረጋገጥ በጽናት ስለታገለና፣ ከህግ ውጭ በአሃዳዊ ፋሽስት የአቢይ አህመድ ኃይል አልገዛም በማለት፣ ዲሞክርሲያዊ ምርጫ ስለአካሄደ ነበር አውዳሚ ወረራና ዘር የማጥፋት ፍጅት ጦርነት የተከፈተበት። ወረራውና የጅምላ ፍጅቱ ዘመቻም ቀጥሏል። የትግራይም ህዝብ ትግል እንዲሁ።

የትግራይ ህዝብ ሆይ፣

በመራራ ትግልና መስዋእትነት ያረጋገጥከውን የራስ እድል በራስ የመወሰን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትህ ቀምተው፥ ማንነትህንና መብትህን ገፈው፣ ህልውናህንም ለመደምሰስ መጠነ-ሰፊ ወረራዎች እያካሄዱብህ ነው።

4 መንግስታትና የክልሎች ልዩ ኃይሎች የተሳተፉበት ትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራና ጦርነት በመሆኑ የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል። ቀደም ሲል ሲገለጽ እንደነበረው፣ አንድ የትግራይ ሻለቃ ለአንድ የጠላት ክፍለጦር ሙሉ ኃይል በመግጠም እጅግ አስደማሚ የሆኑ ጀብድና ጀግንነት ተመዝግበዋል። ከሰሜኑ እዝ የተገኘውን አቅም በመጠቀም በጠላት ላይ ከባድ የማተርያል፣ የሰውና የሞራል ኪሳራዎች አድርሰናል። ይኹንና በኃይል አለመመጣጠን ምክንያት፣ ጊዚያዊ ወታደራዊ ብልጫ ስላገኙ፣ ይህንን ሚዛን ለመለወጥ የመመከት ትግላችንን አጠናክረን እያስቀጠልን እንገኛለን።

ክቡራን እና ክቡራት፣

እነዚህ “የትግራይን ህዝብ አጎሳቁለን፣ ቁም ስቅል አሳይተን፣ ንብረቱን ዘርፈን ወደ ኋላ እንመልሰዋለን” ብለው ከንቱ ልፋት የሚለፉት፣ የማይገባቸው ነገር አለ። ከትግራይ ህዝብ ፈጽመው ሊወስዱት የማይቻላቸው አንድ መሰረታዊ ሃብት እንዳለ አልገባቸውም። የትግራይ ህዝብ ትልቁ ሃብት በኮተትና ግሳንግስ የሚገለጽ ቁሳዊ ሃብት ሳይሆን በማንም ሊዘረፍ የማይችል፣ በያንዳንዱ የትግራይ ሰው ጭንቅላት ላይ ያለው የአስተሳሰብ ብልጫና አቅም ነው። በትግራይ ህዝብ የሚገኝ አቅም ማንም ወራሪ ኃይል ሊመኘው እንጂ ሊወስደው የሚችል ነገር አይደልም።

የትግራይ ህዝብ አቅም በፈቀደለት ልክ ተምሮ፣ በአስተሳሰብ ለውጥና ስልጣኔ ወደፊት ተራምዶ ያረጋገጠው እውነታ፣ ኑሮ የሚለወጠውና እድገት የሚመጣው የሰው ንብረት በመዝረፍ ሳይሆን፣ ጥረህ ግረህ፣ ሌት ተቀን በትጋት ተሰርቶ መሆኑን ነው። በእምነት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭም በዚህ አስተሳሰብ ኑሮውን የቀየረ ህዝብ ነው። ይህ ሃብትና አቅም ማንም የማይወስድበት ቀዋሚ ጥሪቱ ሆኗል። አሁን ደግሞ ተጨማሪ እልህና ወኔ ሰንቆ፣ ወደንበረበት ደረጃ ለመመለስና፣ የሚጎድሉትን ለመሙላት ረዥም ጊዜ የማይወስድበት ህዝብ ነው። በወራሪዎቹ መሪዎችና ሰራዊታቸው አእምሮ ያለው ያረጀ ያፈጀ ክፉ እሳቤ የሚሳካ አይደለም። እየፈፀሙት ያለው ውድመት ቂምና ቁርሾ ለመተው ካልሆነ በቀር፣ ከእንግዲህ ወዲያ ትግራይ ወደ ኋላ ትመለሳለች ማለት የቀን ቅዠት ነው።

ክቡራን እና ክቡራት፣

ትግሉ ከፍተኛ ዋጋ ጠይቋል። የትግራይ መስራች አባላት ከሚባሉት፣ ላለፉት 45 ዓመታት ከያዙት ህዝባዊ መሰመር ፈቅ ሳይሉ የታገሉና የመሩ፣ ያተገሉና ብዙ ድል ያስመዘገቡ አዛውንት ነባር ታጋዮች፣ በዚህ የወረራ ጦርነት በጠላት እጅ ተጎደትውብናል። ከባድ መስዋእትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉም ይገኛሉ። የነዚህ ጀግኖቻችን መስዋእትነት የበለጠ ቁጭትና እልህ ያሰንቀናል እንጂ ፈጽሞ ከትግላችን የሚያቆመን አይሆንም።

ህዝባቸውን እየመሩ ወይም ከሚታገል ህዝባቸው ጋር እየተነቀሳቀሱ የወደቁና የተሰው እነዚህ ጀግኖች በጣም እድለኞች ናቸው። በያዙት መስመር ጸንተው፣ ለህዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ሳያጓድሉ በመሰዋታቸው፣ ስለነሱ እጅግ ከፍ ያለ ክብር ኩራት ይሰማናል። በነዚያ በርከት ያሉ ዘመናት በሙሉ፣ ለህዝብ ያለህን ታማኝነት እንደያዝክና እንደጠበቅክ መሰዋት ማንም እንዲሁ የማያገኘው የክብር ክብር ነው። በመሆኑም ነው፣ ታላላቅና ነባር መሪዎቻችን መስዋዕት በከፈሉበት ማግስት ሳይውል- ሳያድር ከፍተኛ እልህና ወኔ ሰንቀው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ጀግኖችና መሪዎች የሚሆኑት ወጣቶች የአዲሱ ዓላማና ታሪክ አካል ለመሆን ወደ ትግሉ ሜዳ እየጎረፉ ይገኛሉ።

የተክበርክ የትግራይ ህዝብ፣

ፋሺስት አቢይ አሕመድ፣ የህግደፍ ስርአትና የትምክሕት ኃይሎች፣ የትግራይን ህዝብ ዘር የማጥፋት ተልእኳቸው ለማሰፈፀም ግንባር ፈጥረው፣ በላይህ ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና ጥፋት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። በትግራይ ያሉ ከተሞችና ገጠሮች ላይ ያለምህረትና ልዩነት ቀንና ሌሊት፣ በከባድ ጦር መሳሪያዎች፣ በማያቋርጥ ድብደባ እየወደሙ ይገኛሉ። ላለፉት 30 ዓመታት ጥረህ ግረህ ያፈራኸውና ያካባትከው ንብረትህ እየወረሩትና እያወደሙት ይገኛሉ። ልጆቹህ አለጥፋታቸው እየታደኑ ይታረዳሉ። ያሰኛቸውን ይረሽናሉ። ያሰቃያሉ። የተቀረው ደግሞ በረሃብና ቸነፈር እንዲመታ፣ ሆን ብለው፣ የሰበሰብከው እህልና ጥሪትህ ብቻ ሳይሆን የከብት መኖና ገለባም ጭምር ጭነው ይወስዳሉ፣ የተቀረውም እሳት ያነዱታል። ከረሃብና መፈናቀል ጋር ተያይዞ ለህመምና በሽታ የተዳረገ የትግራይ ሰው ካለም፣ ታክሞ እንዳይድን በማለት ትግራይ ውስጥ የሚገኙቱን መድሃኒቶች በሙሉ እየዘረፉ ይወስዱታል። ያልወሰዱት መድሃኒትና የህክምና መገልገያም በእሳት ያጋዩታል። ይኽ በሙሉ አቅማቸው የትግራይን ህዝብ ለመፍጀት እየተረባረቡ ስለመሆናቸው ግልጽ አስረጅ ነው።

እነዚህ ወራሪዎችና ፋሽሽቶች በትግራይ መሬት የሚቆዩባቸው ቀናት በሙሉ የጥፋትና እልቂት ጊዜ እንደሆነ በመገንዘብ፣ ህዝባችን ያላ አንዳች ልዩነት፣ በጠላቶችህ ላይ የጀመርከውን ትግል አጧጡፈህ እንድትቀጥልና ወርቃማ ድሎችህን በፍጥነት እውን እንድታደርግ ጥሪየን አቀርባለሁ።

የተከበርከው የትግራይ አርሶ አደር፣

ጠላቶቻችን፣ በእጃቸው ያለና የሌለ እሳት ባንተ ላይ አዝንበዋል። ይኹንና ይህ ሁሉ የጥፋት እሳት አልፈህ፣ በህዝባዊ መስመርህ ላይ ጸንተህ፣ ትግልህን በማስቀጠልህ፣ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች ከፍ ያሉና ታሪካዊ ናቸው። የጠላቶቻችን በደልና ግፍ ሞልቶ ቢፈስም፣ ከትግል መንገድህ ፈቅ እንደማትል በተግባር አሳይተሃል። ልጆችህን መርቀህ ለትግሉ አሰልፈህ፣ ርብርብህን አጠንክረህ ትገኛለህ። በድምሩ፣ “ትጥቃችን ከጠላቶቻችን፣ ስንቃችን ከህዝባችን” በሚለው የታወቀውና የቆየው መርህ መሰረት ልጆችህን በመመገብና በመንከባከብ እየተወጣኸው ያለኸውን ሃላፊነት ከፍ ያለ፣ ልዩ ክብርና ስፍራ የሚገባው ነው። እናም ልጆችህ፣ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ አብረን የማይቀረው ድል ድረስ እንደምንጓዝ ላርጋግጥልህ እወዳለሁ።

በየከተማው ያለኸው ህዝባችን፡

በትግራይና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ያለኸው ህዝባችን፣ በወራሪዎቹ የተለያዩ በደሎችና ስነልቦናዊ ጥቃቶች ሰላባ ብትሆንም፣ ሳትንበረክክና በጠላት ጉያ ውስጥ ሆነህም ቢሆን የመታገል መንፈስህ ቀጥሏል። በጠላቶቻችን ላይና የነሱ ተላላኪ ባንዳዎች ላይ የቀጠልከው ትግል የሚደነቅ ነው። በመሆኑም፣ ጠላቶቻችን በጠሩት የሰብሰባ መድረኮች ላይ ሳይቀር የምታካሂዱት መርህን መሰረት ያደረገ ትግል አበጃቹህ የሚያሰኝ ነው። መታዘብ ለቻለ፣ የትግራይ ህዝብ አንገቱን የሚደፋ ሳይሆን፣ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ጭምር የመጣውን ግፈኛ የሚጋፈጥ፣ ባመነበት ላይ ጸንቶ የሚታገል እንደሆነ አስመስክራችኋል። ለማንነታችሁና ለመብታችሁ የምታደርጉት ትግል፣ ጠላቶቻችን ተጠራርገው እስኪወጡ ድረስ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉበት ጥሪየን አቀርባለሁ።

የተከበራቹህ የትግራይ የመከታና መከለከያ ኃይሎች፣

የትግራይ ጠላቶችና ወራሪዎች፣ እኛን ከምድረ-ገጽና ከህልውና ለመፋቅ፣ አንድ ላይ ተጠራርተውና ግንባር ፈጥረው፣ የትግራይ አዳጊ ትውልድን በደረሱበት እየረሸኑና እያረዱ፣ ያላደረጉት ወንጀልና ያልፈጸሙት ግፍ የለም። የወጣቶቻችን አካል በነዚህ አረመኔዎች በየቦታው በስለት እየተተለተለና በእሳተ እየተቃጠለ እንደዘበት ይጣላል። በዚህም ምክንያት ከቀያችሁ እየሸሻችሁ እየተሰደዳችሁ በየቦታው የምትንከራተቱ ውጣቶች እነዚህ አረመኔዎች እስካሉ ድረስ የሰላም ኑሮ አይኖራችሁም። ከትምህርት መአድ ተስተጓጉላቹህም የጨለማ ጊዜ ለማሳለፍ ተገዳቹህ ትገኛላችሁ። እነዚህ ወራሪ ኃይሎች በትግራይ ምድር በቆዩበት ጊዜ የሚያደርሱት ግፍና ጥፋት ብቻ ሳይሆን የድምሰሳ ዘመቻቸው በመጪው የትግራይ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚያጠላው መጥፎ ጥላ ተገንዝባችሁ በዲጂታል ወያነና በሌሎች አውዶች የምታካሂዱት ትግልና ርብርብ የሚያኮራ ነው። እናንተ በዚች ፈታኝ ወቅት አደራችሁን ሳትበሉ በትግላችሁ የቀጠላችሁ የአዲሱ ትውልድ ወጣቶች፣ እናንተም ታሪክ እየሰራችሁ ነው። ትግራይም በናንተ ኮርታለች። ትግላችሁን አበርትታችሁ ቀጥሉበት፣ ሌሎቻችሁም በፍጥነት የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ። የወራሪዎቹን እድሜ ፈጠነን እናሳጥረው ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ።

ክቡራት የትግራይ ሴቶች፣

የፋሽስቱ አቢይ አህመድ ቡድኖችና የኢሳያስ ህግደፍ ስርዓት የትግራይ ህዝብ ላይ ዘር የማጥፋት አላማ ያነገበው ጅምላዊ ፍጅት፣ ግፍና ወንጀል ለመናገሩ አይደለም ለመስማትም የሚቀፍ እጅግ መራራ ጥቃት ነው። የትግራይ ሴቶች በወራሪዎቹ ኃይሎች፣ በተናጠልና በጋራ የሚደፈሩበት እጅግ አሰቃቂ ሁኔታዎች እያለፍን ነው። እናትና ልጅ በጋራ ይደፈራሉ። የወለዳቹኋቸው ለግለጋ ወጣቶች ለጥይትና ለስደት ይዳረጋሉ። ሃብትና ንብረት ይዘረፋል፣ ይወድማል። የትግራይ ጠላቶች መሬታችን ላይ የሚቆዩበት እያንዳንዷ ቀን፣ በትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ለተጨማሪ ጊዜ እንዲቀጥል መፍቀድ ማለት ስለሆነ በያለችሁበት ሆናቹህ በቻላችሁት ሁሉ ተደራጅታችሁ ጠላትን ታገሉ። እድሜውና አቅሙ የፈቀደለት ሁሉ ለትግል እንዲሰለፍ እንድታደርጉና በሁሉም መንገድ የጠላት እድሜ እንድናሳጥር ጥሪየን አቀርባለሁ።

የተከበራቹህ የትግራይ ዲያስፖራ፣

በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣው የተቀናጀና የተናበበ ዘር የማጥፋት ዘመቻና ወንጀል ተገንዝባችሁ፣ ህዝባችሁን ለመታደግ የህዝባችሁን አምባሳደሮች ሆናችሁ የምታደርጉት ትግል የሚደነቅ ነው። ይሁንና ትግሉ ተጀምሯል እንጂ አልተገባደድም። የትግራይ ህዝብ የራስ እድል በራስ የመወሰን መብት ሙሉ በሙሉ እስኪረጋገጥ ድረስ የሚቀጥል ነው። ስለሆነም በአንድ በኩል፣ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል የዓለም ማ/ሰብ በሚገባ እንዲያውቀው የተጠናከረ ስራ እንድትሰሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜያችሁ፣ እውቀታችሁና ገንዘባችሁን በማስተሳሰር የትግራይ ህዝብን ትግል ለማጠናከር የጀመራችሁትን አስተዋጽኦ ከፍ በማድረግ የጀመራችሁትን አኩሪና ታሪካዊ ኃላፊነት እሰከመጨረሻው ትወጡ ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ።

የተከበራቹ የዓለም ማ/ሰቦች፡

ፋሺስት አብይ አሕመድ፣ የኤርትራን ሰራዊት ጨምሮ ሌሎች የባእድ ኃይሎችንም ጋብዞ ምንም ጥፋት የሌለበትን የትግራይን ህዝብ እየቀጠቀጠው ነው። የጥፋት ኃይሎቹ፣ የትግራይን ህዝብ በጥይትና በረሃብ ለመጨረስ ያለ እረፍት ሌትና ቀን የፍጅት ተልእኳቸውን ቀጥለዋል። በመሆኑም፣ የትግራይ ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ንጹሃን ሰዎች በየተገኙበት ይረሸናሉ። የትግራይ ሴቶች በተናጠልና በደቦ ይደፈራሉ። የትግራይ ሰዎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች በከፋ መገለጫና አኳሃን ይጣሳሉ፣ ይገፈፋሉ። የትግራይ መንደሮችና ዓብያተ እምነቶች፣ የትግራይ ሰራዊት ይኑርበት አይኑርበት ሳይገዳቸው የቦምቦችና የመድፎ ዒላማ ይደረጋሉ። ውድና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶችም ይወድማሉ፣ ይዘረፋሉ። በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዳለ ከቀየው ወጥቶና ተፈናቅሎ የመከራ ኑሮ ይኖራል። የቤት እንስሳ ሳይቀሩ መጠለያ አጥተው እየተሰደዱ ነው። በአጠቃላይ በትግራይ ህዝብ ላይ የለየለት የጅምላ ፍጅትና ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ በዕቅድ እየተሰራበት ነው። ይኽ ዓይነት ወንጀል እላዩ ላይ የተበየነበት ህዝብ ደግሞ የፈጸመው ወንጀል ስላለ ሳይሆን የራሱን አስተዳዳሪዎች ለመምረጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስላካሄደ ብቻ ነው። ሰለሆነም፣ ይኽንን በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል በግልጽ እንድትቃወሙና እንድታወግዙ፣ እንዲሁም እየተፈፀመ ያለውን ወንጀል እንዲጣራና በፈጻሚዎቹ ወራሪ ኃይሎቹም ላይ የሚቻለው ህጋዊ እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ፣ በተለይም ደግሞ የዚህ ፍጅትና ወረራ አስፈጻሚ የሆኑት መሪዎች አብይ አሕመድና ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አለማቀፍ የወንጀል ፍ/ቤት ፊት እንዲቀርቡ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ በትግራይ ስም ጥሪየ አቀርባለሁ።

ክቡራት እና ክቡራን፡

ያለፉት የትግራይ ትውልዶች አዕላፍ ወራሪዎችንና የባዕድ ኃይሎችን አሳፍረው የመለሱት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ ሚሳይሎችና ታንኮችን ታጥቀው አልነበረም። “የህዝብ መብት አሳልፈን አንሰጥም፣ አንምበረከክም” በሚል የዓላማ ጽናትና አንድነት ይዘውና በመርህ ታግለው ነው። እኛም የገጠመንን ወራሪ ኃይል ለመመከትና ለማሸነፍ እምነታችን፣ ጽናታችንና አንድነታችንን ይዘን ጠላቶቻችንን ለመግጠም፣ የትግራይ ህዝብ ታሪክና ክብር እንደ ደመቀ ይቀጥል ዘንድ የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ሆነን ትግላችንን ማጧጧፍ ይገባናል። ያገጠመው ችግርና ውጣ ውረድ፣ እንዲሁም እንግልት አልፈን፣ የመመከት አቅማችንን አጎልበተን፣ ማንኛውም የመጣን የጠላት ኃይል በድል ማሸነፍ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም።ጠላቶቻችን የመከላከል አቅማችን እየተጠናከረ በመሄዱ ስለተደናገጡ፣ አቅማቸውን እንደ አዲስ አሰባስበው፣ ከባድ ወረራ ማካሄድ ጀምረዋል። ይሁንና አሁን ተጀምሮ ያለውን ህዝባዊ ጦርነት፣ ጠላቶችን በመደምሰስና በመቅበር ለድል መብቃቱ የማይቀር ነው።

ካለፉት ባዕዳውያን ወራሪ ሃይሎች ተሞክሮ ያላቸው አማራጭ ከመደምሰስ የተረፉት ጓዛቸውን ጠቅልለው ከትግራይ ሲወጡ ብቻ ነው። ያሁኖቹ ወራሪዎችም ከመደምሰስ የሚድኑት ኮተታቸውን ይዘው ከትግራይ ለቀው የወጡ እንደሆነ ነው። ያ ካልሆነ እኛ ከመሬታችን እና ከቀያችን ለቀን የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለንምና የተሟላ ድል እስክንቀዳጅ ህዝባዊ ጦርነት ከማፋፋም ወደ ኋላ እንደማንል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል። ድላችንም ጠላቶቻችንን በመቅበር የግድ በእጃችን መሆኑን ለሁሉም እናረጋግጣለን።

ድል ለትግራይ ህዝብ!
ውድቀት ለትግራይ ህዝብ ጠላቶች!
ለትግራይ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንታገል!
ዘላለማዊ ክብር ለቀድሞ እና ለአሁኖቹ ጀግኖች ስማእቶቻችን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *