የእስረኞች አጣብቂኝ (Prisoner’s Dilemma)

በኢኮኖሚስቶች ዓለም የእስረኞች አጣብቂኝ የምትባል ፅንሰ ሀሳብ አለች። የማትገባበት ቦታ የለም። በወልና በተናጠል የሚደረጉ ውሳኔዎች ጥንካሬና ድክመት ለመመዘን እንደመነሻ የምንጠቀምባት ጽንሰሀሳብ ነች።

ለምሳሌ ሰዎች ስንባል ብዙ ጊዜ የመተባበር ችግር እንዳለብን ይታወቃል። ለምን? የሚለውን ጥያቄ በዘዴ ለማወቅ ይህ ፅንስ ሀሳብ ይረዳል። ላለመተባበር ምክንያቱ ከታወቀ ምንጩ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ፍንጭ ይሰጣል። ብዙ ግዜ መነሻ ምክንያቶቹ ሊሆኑ የሚችሉት የመረጃ ልዩነት (information asymmetry)፣ ውሳኔው የሚያስከትለው ኪሳራ ወይም ጥቅም(incentive/payoff structure)፣ ከቀድሞ ውሳኔዎች የመማር እድል፣ የተሳታፊዎች ብዛት ወዘተ ናቸው። ከነዚህ መካከል መነሻ ምክንያቱ የትኛው እንደሆነ ሲታወቅ ቀጣይ ውሳኔ ትብብር ላይ የተመሰረተና የብዙሀኑን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሆን የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይረዳል።

ዝነኛ በሆነችው ምሳሌ ጉዟችንን እንጀምር።

ሁለት ግለሰቦች በአንድ ወንጀል ተጠርጥረው ህግ ፊት ቀርበዋል። ሁለቱም ለየብቻ ታስረው በተናጠል ምርመራ እየተደረገላቸው ነው። ለእያንዳንዳቸው የሚከተሉት 3 አማራጮች ቀረቡላቸው፣

1 አንተ ካመንክና ተባባሪህ ካላመነ 1 ዓመት ብቻ ትቀጣለህ።

2 አንተ ካላመንክና ተባባሪህ ካመነ 10 ዓመት ትቀጣለህ (እርሱ 1 ዓመት ብቻ ይቀጣል ማለት ነው)።

3 ሁለታችሁም ካመናችሁ  ስላመናችሁ 1 ዓመት ተቀንሶላችሁ 5 ዓመት ብቻ ትቀጣላችሁ።

(4 ሁለቱም ካላመኑ ፖሊስ በራሱ መንገድ ማስረጃ ይፈልጋል። ማረጋገጥ ከቻለ 6 ዓመት ይቀጣቸዋል። ካልቻለ በ48 ሰዓት ውስጥ ይለቃቸውና የማጣራት ስራውን ይሰራል። ምንም ማስረጃ ከሌለው ነጻ ይሆናሉ።)

ምርጫውን ላንተ ትቸዋለሁ ብሎ ውልቅ ይላል። ትንሽ ጊዜ ለመስጠት ያህል። ተመልሶ ሲመጣ ይጠይቃል። ብልጦች ከሆኑ የሚያዋጣቸው አለማመን ነው። ነገር ግን አብዛኛውን ግዜ አእምሯችን እንደዛ አይሰራም።

ተጠርጣሪው አመነ።

ምክንያቱም ጓደኛው ካመነና እርሱ ካላመነ፣ ጓደኛው በ1 ዓመት ሲገላገል፣ እርሱ 10 ዓመት ሊልፍ ሆነ። ሁለቱም ካመኑ እያንዳቸው የሚጠብቃቸው 5 ዓመት ነው። ይሻላል። እርሱ አምኖ ጓደኛው ካላመነ ደግሞ ጸሃይ ወጣለት ማለት ነው። በ1 ዓመት እስራት ይገላገላል፣ ጓደኛው ደግሞ 10 ዓመት ይልፋል። ስለዚህ ካለማመን ማመን ይሻላል። ለምኔ? ብሎ ጓደኛውን አሳልፎ ለመስጠት ወስኗል።

ክፋቱ ያኛውም በተመሳሳይ መንገድ፣ ተመሳሳይ አመክንዮ በማቅረብ አምኗል። ስለዚህ ሁለቱም 5 ዓመታቸውን ጠጡ። ሁለቱም እንደተማማሉት ክደው ጭጭ ቢሉ ፖሊስ ማስረጃ እስኪያሰባስብ ነጻ ይለቃቸው ነበር። ማስረጃ ፍለጋ ይዳክራል፤ እስኪያገኝ ድረስ ነጻ ናቸው። በግዜ ገደቡ ማስረጃ ካላቀረበ ደግሞ ክሱ ውድቅ ሆኖ ነጻ ይሆናሉ። ከማመን ይልቅ ባለማመን የመታሰር እድላቸው ዝቅተኛ ይሆን ነበር። ነገር ግን ፖሊሱ ስስ ብልታቸውን ያውቃልና (ኢኮኖሚክስ ተምሯልና ) በዘዴ ጠልፎ መረቡ ላይ ጣላቸው። ለ5 ዓመት አሰራቸው።

ይህ ችግር በኢኮኖሚክስ ቋንቋ coordination problem ይባላል። ምንጩ የመረጃ እጥረት ነው። በህልውና ጥያቄ ላይ አንደኛው የሚያስበውን ሌላኛው ሊያውቅ አይችልም። እንደ ቁማር አስልቶ ይገምታል ብቻ። እኔ ብሆን በሱ ቦታ ምን አደርግ ነበር እያለ በተዘዋዋሪ የራሱን ባህሪ ያጠናል። ከዛ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውምና፡ በተለይ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ የተያዙት። በተደጋጋሚ የተያዙ ከሆነ፣ ከቀድሞ ስህተታቸው ተምረው፣ መተማመንን ያዳብራሉ። ይተባበራሉ። በጋራ መካድ እንደሚያዋጣቸው ያውቃሉ። የcoordination problemን ለመፍታት አንዱ ቁልፍ መንገድ ከቀድሞ ስህተት መማር ነው።

ከመነሻው የግል ጥቅምን ከማሳደድ ይልቅ ትብብር ላይ የተመሰረተ የኑሮ ዘይቤ መከተል የሚቀናን ከሆነ ይህ ችግር አያጋጥመንም።  እያንዳንዳቸው ሰለፊሽ በሆነችው መንገድ አስልተው ባያምኑና ጭጭ ቢሉ ኖሮ 5 ዓምት ባልጠጡ ነበር። ቢያንስ ማስረጃ እስኪገኝ ድረስ ነጻ ናቸው። ሙሉ በሙሉ ነጻ የመሆን እድላቸውም ከፍተኛ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ በክህደት ራሳቸውን አያስገምቱም ነበር። ጸጸቱ ቀላል ነው እንዴ? ነገር ግን በተናጠል ያሰሉት የግል ጥቅምን ማስፋት ነው። ወደ 1 ዝቅ ለማለትና አስሯን ለማስቀረት። አስሯን ከራሱ ለማስቀረት ሲያሰላ በተዘዋዋሪ ጓደኛው ላይ ለመወርወር ወስኗል። አሳልፎ መስጠትና አለመተማመን፣ ተንጋሎ እንደመትፋት ነው። ተመልሶ ለራስ ይተርፋል።

ይህ የመተባበር ችግር በተለይ በኛ በኢትዮጵያውያን በሁሉም መስክ ዘውትር ይታያል። ፖለቲካችን በመተማመን ወደፊት መገስገስ ሳይሆን በመጠላለፍ መንገዳገድ ይቀናዋል። ማህበራዊ ህይወታችን መተማመን ላይ የተመሰረተ አይደለም። እንዳውም ለትብብር ቅርብና ቀና የሆኑ ሰዎችን እንደ ጅል ማየት ይቀናናል። የምናደንቀው ብልጦችን ነው። የራሳቸውን የማያስነኩ የሌላውን መመንተፍ  የተካኑ። ይህ በተለይ በከተሞች አካባቢ ይብሳል። ከተሜነት ጩልሌነት ነው እንዴ ያስብላል። በጋራ የምንጠቀምባቸው ነገሮችን ማየት ይቻላል። መንገድ ላይ እንጸዳዳለን። ያልተከልነው ደን እንመነጥራለን። የህዝብ ካዝና እናራቁታለን። የመንግስት መኪና ስንጠቀም ነዳጅ እንደውሃ ይረክስብናል። …

በአንድ ወቅት በደንብ ያጠናን አሜሪካዊ የደረሰበትን ድምዳሜ በማካፈል ለዛሬ ያዘጋጀሁትን አጭር ጽሁፍ ልቋጭ።ሊያስቆጣን ቢችልም በውስጡ የማንክደው ሀቅ ስለያዘ በቀናነት እንየው፥

“Ethiopians tend to view the life game as zero-sum, non-shared sum, and yielding at best a limited payoff. This view results in a set of survival strategies based on self-protection, deception, and revenge aimed either at maintaining the status quo or advancing oneself at the expense of others. Perceived opportunities for initiative and cooperation in service to the community are limited. Personal efficacy is perceived as present in interpersonal exchanges, but not in exchanges with the impersonal environment.”  (David Korten 1971.  The Life Game: Survival Strategies in Ethiopian Folktales.)

የዴቪድ ኮርተን ድምዳሜ የተጋነነ ነው የሚል አይጠፋም። እኔም የምጋራው ነው። ነገር ግን ፖለቲካዊና አብዛኛውን ማህበራዊ ህይወታችን በተለይ ከተማ አካባቢ ያለውን ማህበራዊ ህይወት የሚገልጽ ነገር እንዳለው መካድ አይቻልም። በገጠሩ አካባቢ ያሉ በትብብር ላይ የተመሰረቱ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች የሚያስተምሩን ነገር ስላለ በሌላ ግዜ እመለስባቸዋለሁ። እስከዛ በሰላም ቆዩኝ!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *