እንደ ገበያ እናስብ

ገበያ አንድ ሰው ያመረተውን ምርት ወይም የሚሰጠውን አገልግሎት ይመዝናል፣ እንደሚዛኑም ዋጋ ይሰጣል እንጂ፣ የሰውን ማንነት አይመዝንም። የአንድ ሰው እምነት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ፍልስፍና፣ ጾታ ወዘተ ለገበያ ግድ የሚሰጠው ነገር አይደለም። ዋናው ጉዳይ ገበያው የሚፈልገውን ምርት አቀረብክ ወይ? የምትሰጠው አገልግሎት የደንበኛውን ፍላጎት ያሟላል ወይ? ነው። ገበያው የሚፈልገውን ምርት ካቀረብክና ደንበኛህ የሚጠብቀውን ፍላጎት ካሟላህ ጥረትህ ዋጋ ያገኛል፣ ካልሆነ ግን ማንም ምንም ብትሆን ዋጋ የለህም።

ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ አርቲስቶች በጠቅላላ ማለት ይቻላል፣ ሲዘፍኑ አማርኛ መቀላቀል ባህል እያደረጉት መጥተዋል። ለ27 ዓመታት የተሰበከው የጠባብ ብሔርተኞች ትርክት፣ በገበያ ሚዛን ቦታ ማጣቱን ያሳያል። አርቲስቶቹና በዙሪያቸው ያሉ ነጋዴዎች እንደ ገበያው ሁኔታ ሲያስቡ፣ አንድን አርቲስት በትውልድ ቋንቋው ብቻ በማዘፈን ገበያቸውን የተወሰነ አድማጭ ላይ ብቻ ከሚገድቡ፣ አማርኛን ቀላቅለው ሁለቱንም ቋንቋ የሚችል ሰፊ አድማጭ ዘንድ ስራቸውን ማዳረስ የበለጠ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው ተገንዝበዋል።

በኔ ግምት ቢያንስ 70% የኢትዮጵያ ህዝብ አማርኛ መስማት የሚችል ይመስለኛል። 10 በመቶ የማይሞላን አድማጭ ታርጌት ከማድረግ፣ ዜማው እንደተጠበቀ ሆኖ ጥቂት የአማርኛ ስንኞችን በመጨመር ብቻ የ70 በመቶውን አድማጭ በር ማንኳኳት በብዙ እጥፍ ትርፋማ ያደርጋል።

ህወሓት በዘር ፖለቲካ ያጠመቃቸው የትግራይ ተወላጆች ግን ይህን ሳይረዱ ለሳምንታት ባለማቋረጥ በእነ አርቲስት ማህሌት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተዋል። አርቲስቶቹ ዘፈናቸው መሀል አማርኛ መቀላቀላቸውን እንደተለመደው ዘረኛ ፖለቲካቸውን ለማራገብ ሲጠቀሙበት ሰንብተዋል። አርቲስቶቹ በነዚህ ጎሰኞች የተቀመጠላቸውን አጥር በጣጥሰው ህዝብን ለማቀራረብ የሚረዳ ስራ ማቅረብ ከመቻላቸውም በተጨማሪ እንጀራቸውን የሚያበስሉበት ገበያ ተኮር አስተሳሰብ ነውና እንዲቀጥሉበት ማበረታታት ተገቢ ነው።

በእርግጥ በዋናነት የሚያበረታታቸው ገበያው ራሱ ነው።

ጥሮ ግሮ የሚበላ ሰው ገበያውን ያሰፋል። እየዘረፈ የሚበላ ሰው ምሽጉን ይገነባል። በብሔር  ስትታጠር፣ የወንጀለኛና ቀማኛ ምሽግ ከመሆነ ያለፈ የምታገኘው ጥቅም አይኖርም ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *